የይሁዳና የብንያም ጠላቶች ከምርኮ የተመለሱት ሰዎች የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በመሥራት ላይ መሆናቸውን ሲሰሙ፣ ወደ ዘሩባቤልና ወደ ቤተ ሰቡ አለቆች መጥተው፣ “እኛም እንደ እናንተ አምላካችሁን የምንፈልግ ነን፤ የአሦር ንጉሥ አስራዶን ወደዚህ ካመጣን ጊዜ ጀምሮ ለርሱ ስንሠዋለት ቈይተናል፤ ስለዚህ ዐብረን ከእናንተ ጋራ እንሥራ” አሏቸው። ዘሩባቤል፣ ኢያሱና ሌሎቹ የእስራኤል ቤተ ሰቦች አለቆች ግን፣ “ለአምላካችን ቤተ መቅደስ እንድትሠሩ ከእኛ ጋራ የሚያገናኛችሁ ምንም ነገር የለም። የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ ባዘዘን መሠረት ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የምንሠራው እኛ ብቻ ነን” ሲሉ መለሱላቸው። ከዚያም የምድሪቱ ነዋሪዎች የይሁዳን ሕዝብ ተስፋ ማስቈረጥና ሥራውንም እንዳይቀጥሉ ማስፈራራት ጀመሩ። ከፋርስ ንጉሥ ከቂሮስ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ እስከ ፋርስ ንጉሥ እስከ ዳርዮስ ዘመነ መንግሥት ድረስ ዕቅዶቻቸውን የሚያሰናክሉ መካሪዎችን በገንዘብ ገዙባቸው። በጠረክሲስ ዘመነ መንግሥት መጀመሪያ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ላይ የጽሑፍ ክስ መሠረቱባቸው። በፋርስ ንጉሥ በአርጤክስስ ዘመን ቢሽላም፣ ሚትሪዳጡ፣ ጣብኤልና ተባባሪዎቹ ወደ አርጤክስስ ደብዳቤ ጻፉ። ደብዳቤው የተጻፈው በአራማይክ ፊደል፣ በአራማይክ ቋንቋ ነበረ። አገረ ገዥው ሬሁምና ጸሓፊው ሲምሳይ በኢየሩሳሌም ላይ ለንጉሡ ለአርጤክስስ እንዲህ የሚል ደብዳቤ ጻፉ፤ ደብዳቤው የተጻፈው፣ ከአገረ ገዥው ሬሁም፣ ከጸሓፊው ሲምሳይ በትሪፖሊስ፣ በፋርስ፣ በአርክ፣ በባቢሎን እንዲሁም በሱሳ ማለትም በኤላማውያን ላይ ዳኞችና ገዦች ከሆኑት ከተባባሪዎቻቸው፣ ደግሞም ታላቁና ኀያሉ አስናፈር አፍልሶ በሰማርያ ከተማና ከኤፍራጥስ ወንዝ ማዶ እንዲሰፍሩ ካደረጋቸው ሌሎች ሕዝቦች ነው። የላኩለት ደብዳቤ ቅጅ ይህ ነው፤ ለንጉሥ አርጤክስስ፣ በኤፍራጥስ ወንዝ ማዶ ከሚኖሩት አገልጋዮችህ የተላከ፤ ከአንተ ዘንድ ወደ እኛ የመጡት አይሁዳውያን ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድ ዐመፀኛና ርኩስ ከተማ እንደ ገና በመሥራት ላይ ናቸው፤ ቅጥሮቿንም እንደ ገና በመሥራትና መሠረቶቿንም በመጠገን ላይ መሆናቸው በንጉሡ ዘንድ የታወቀ ይሁን። ከዚህም በላይ ይህች ከተማ ከተሠራች፣ ቅጥሮቿም እንደ ገና ከተገነቡ፣ ቀረጥና እጅ መንሻ ወይም ግብር እንደማይከፍሉ፣ የቤተ መንግሥቱም ገቢ እንደሚቀንስ በንጉሡ ዘንድ የታወቀ ይሁን። አሁንም እኛ ስለ ቤተ መንግሥቱ ስለሚገደን፣ የንጉሡም ክብር ሲነካ ዝም ብሎ ማየት ተገቢ ሆኖ ስላላገኘነው፣ ይህ ነገር በንጉሡ ዘንድ የታወቀ እንዲሆን ይህን መልእክት ልከናል፤ ስለዚህ በአባቶችህ ቤተ መዛግብት ምርመራ ይደረግ፤ በእነዚህ መዛግብት ውስጥ ይህች ከተማ ዐመፀኛ ከተማ እንደ ሆነች፣ ነገሥታትንና አውራጃዎችን የጐዳችና ከጥንት ጀምሮ የዐመፅ ጐሬ ስለ መሆኗ ማስረጃ ታገኛለህ፤ እንግዲህ ከተማዪቱ የተደመሰሰችው በዚህ ምክንያት ነው። ይህች ከተማ ተመልሳ የምትሠራና ቅጥሮቿም እንደ ገና የሚገነቡ ከሆነ፣ ከኤፍራጥስ ማዶ ምንም ነገር እንደማይኖርህ፣ ንጉሥ ታውቅ ዘንድ እንወድዳለን።
ዕዝራ 4 ያንብቡ
ያዳምጡ ዕዝራ 4
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዕዝራ 4:1-16
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች