የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሕዝቅኤል 36:22-32

ትንቢተ ሕዝቅኤል 36:22-32 አማ54

ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በመጣችሁባቸው በአሕዛብ መካከል ስላረከሳችሁት ስለ ቅዱስ ስሜ ነው እንጂ ስለ እናንተ የምሠራ አይደለሁም። በአሕዛብም ዘንድ የረከሰውን፥ በመካከላቸው ያረከሳችሁትን ስሜን እቀድሰዋለሁ፥ በዓይናቸውም ዘንድ በተቀደስሁባችሁ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ አሕዛብ ያውቃሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ከአሕዛብም መካከል አወጣችኋለሁ ከየአገሩም ሁሉ እሰበስባችኋለሁ ወደ ገዛ ምድራችሁም አመጣችኋለሁ። ጥሩ ውኃንም እረጭባችኋለሁ እናንተም ትጠራላችሁ፥ ከርኵሰታችሁም ሁሉ ከጣዖቶቻችሁም ሁሉ አጠራችኋለሁ። አዲስም ልብ እሰጣችኋለሁ አዲስም መንፈስ በውስጣችሁ አኖራለሁ፥ የድንጋዩንም ልብ ከሥጋችሁ አወጣለሁ፥ የሥጋንም ልብ እሰጣችኋለሁ። መንፈሴንም በውስጣችሁ አኖራለሁ በትእዛዜም አስሄዳችኋለሁ፥ ፍርዴንም ትጠብቃላችሁ ታደርጉትማላችሁ። ለአባቶቻችሁም በሰጠኋት ምድር ትኖራላችሁ፥ ሕዝብም ትሆኑኛላችሁ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ። ከርኵሰታችሁም ሁሉ አድናችኋለሁ፥ እህልንም እጠራዋለሁ አበዛውማለሁ ራብንም አላመጣባችሁም። ደግሞም የራብን ስድብ ከአሕዛብ ዘንድ እንዳትሸከሙ የዛፍን ፍሬና የእርሻውን ቡቃያ አበዛለሁ። ክፉውን መንገዳችሁንና መልካም ያይደለውን ሥራችሁንም ታስባላችሁ፥ ስለ በደላችሁና ስለ ርኵሰታችሁም ራሳችሁን ትጸየፋላችሁ። ይህን የሠራሁ ስለ እናንተ እንዳይደለ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ስለ መንገዳችሁ እፈሩና ተዋረዱ።