ትንቢተ ሕዝቅኤል 12:21-28

ትንቢተ ሕዝቅኤል 12:21-28 አማ54

የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ በእስራኤል ምድር፦ ዘመኑ ረዝሞአል ራእዩም ሁሉ ጠፍቶአል የምትሉት ምሳሌ ምንድር ነው? ስለዚህ እንዲህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ይህን ምሳሌ አስቀረዋለሁ በእስራኤልም ዘንድ ደግሞ ምሳሌ አድርገው አይናገሩትም፥ አንተ ግን፦ ዘመኑና የራእዩ ሁሉ ነገር ቀርቦአል በላቸው። ከዚህም በኋላ በእስራኤል ቤት መካከል ከንቱ ራእይና ውሸተኛ ምዋርት አይሆንም። እኔ እግዚአብሔር ነኝ፥ እናገራለሁ የምናገረውም ቃል ይፈጸማል፥ ደግሞም አይዘገይም፥ እናንተ ዓመፀኛ ቤት ሆይ፥ በዘመናችሁ ቃሌን እናገራለሁ እፈጽመውማለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ እነሆ፥ የእስራኤል ቤት፦ ይህች የሚያያት ራእይ ለብዙ ዘመን ናት፥ እርሱም ለሩቅ ወራት ትንቢት ይናገራል ይላሉ። ስለዚህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የምናገረው ቃል ይፈጸማል እንጂ ከቃሌ ሁሉ ደግሞ የሚዘገይ የለም፥ ይላል እግዚአብሔር።