ትንቢተ ሕዝቅኤል 12:21-28

ትንቢተ ሕዝቅኤል 12:21-28 አማ05

እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! ራእዩ ሁሉ ተግባራዊ ሳይሆን ቀኖቹ ተራዘሙ ተብሎ ስለ እስራኤል ምድር የሚነገረው ይህ ምሳሌ ምንድን ነው? እኔ ልዑል እግዚአብሔር ስለዚህ ጉዳይ የምለውን ንገራቸው፤ ይህ ምሳሌ እዚሁ ላይ እንዲያበቃ አደርገዋለሁ፤ ዳግመኛም በእስራኤል አይነገርም፤ በዚህ ፈንታ ‘እነሆ ጊዜው ደርሶአል፤ የትንቢቱም ቃል ሁሉ ሊፈጸም ነው!’ ብለህ ንገራቸው። “በእስራኤል ሕዝብ መካከል ሐሰተኛ ራእይ ወይም ሟርት ከእንግዲህ ወዲህ ከቶ አይነገርም። እኔ እግዚአብሔር በቀጥታ እናገራለሁ፤ የምናገረውም ቃል ሁሉ ይፈጸማል፤ ከእንግዲህ ወዲህም ከቶ አይዘገይም፤ እናንተ ዐመፀኞች ‘በእናንተ ላይ አመጣለሁ’ ብዬ በማስጠንቀቅ የተናገርኩትን ሁሉ በሕይወታችሁ ዘመን እንዲፈጸም አደርጋለሁ፤ ይህን የተናገርኩ እኔ ልዑል እግዚአብሔር ነኝ።” እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! እስራኤላውያን የአንተ ራእይና ትንቢት ‘ከብዙ ዘመን በኋላ የሚፈጸም ነው’ ብለው ይናገራሉ፤ ስለዚህ እኔ እግዚአብሔር የምላቸውን ንገራቸው፤ እኔ የተናገርኩት ሁሉ ይፈጸማል፤ ከቶም አይዘገይም፤ ይህን የተናገርኩ እኔ ልዑል እግዚአብሔር ነኝ።”