የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘጸአት 28

28
1አንተም ወንድምህን አሮንን ከእርሱም ጋር ልጆቹን ከእስራኤል ልጆች መካከል ለይተህ ካህናት ይሆኑልኝ ዘንድ ወደ አንተ አቅርብ፤ አሮንን የአሮንንም ልጆች፥ ናዳብን አብዩድንም አልዓዛርንም ኢታምርንም፥ አቅርብ። 2የተቀደሰውንም ልብስ ለክብርና ለጌጥ እንዲሆን ለወንድምህ ለአሮን ሥራለት። 3አንተም ካህን ሆኖ እንዲያገለግለኝ አሮን ቅዱስ ይሆን ዘንድ ልብስ እንዲሠሩለት የጥበብ መንፈስ ለሞላሁባቸው በልባቸው ጥበበኞች ለሆኑት ሁሉ ተናገር። 4የሚሠሩአቸውም ልብሶች እነዚህ ናቸው፤ የደረት ኪስ ኤፉድም ቀሚስም ዝንጕርጕር ሸሚዝም መጠምጠሚያም መታጠቂያም፤ እነዚህም ካህናት ይሆኑልኝ ዘንድ ለወንድምህ ለአሮን ለልጆቹም የተቀደሰ ልብስ ያድርጉ። 5ወርቅንም፥ ሰማያዊና ሐምራዊ ቀይም ግምጃ፥ ጥሩ በፍታም ይውሰዱ። 6ኤፉዱንም በብልሃት የተሠራ በወርቅና በሰማያዊ በሐምራዊም በቀይም ግምጃ ከተፈተለ ከጥሩ በፍታም ብልህ ሠራተኛ እንደሚሠራ ያድርጉ። 7ሁለቱ ወገን አንድ እንዲሆን በሁለቱ ጫንቃ ላይ የሚጋጠም ጨርቅ ይሁን። 8በላዩም መታጠቂያ ሆኖ በብልሃት የተጠለፈው የኤፉድ ቍድ እንደ እርሱ ከእርሱም ጋር አንድ ይሁን፤ ከወርቅና ከሰማያዊ ከሐምራዊ ከቀይ ግምጃም ከተፈተለ ከጥሩ በፍታም የተሠራ ይሁን። 9ሁለትም የመረግድ ድንጋይ ወስደህ የእስራኤልን ልጆች ስም ስማቸውን ቅረጽባቸው፤ 10እንደ አወላለዳቸው ስድስት ስም በአንድ ድንጋይ፥ የቀረውንም ስድስቱን ስም በሌላው ቅረጽ። 11በቅርጽ ሠራተኛ ሥራ እንደ ማኅተም ቅርጽ አድርገህ የእስራኤልን ልጆች ስም በሁለት ድንጋዮች ቅረጽ በወርቅም ፈርጥ አድርግ። 12የእስራኤል ልጆችም የመታሰቢያ ድንጋዮች ይሆኑ ዘንድ ሁለቱን ዕንቁዎች በኤፉዱ ጫንቃዎች ላይ ታደርጋለህ፤ አሮንም በሁለቱ ጫንቃዎች ላይ ለመታሰቢያ ስማቸውን በእግዚአብሔር ፊት ይሸከማል። 13-14የወርቅም ፈርጦች ሁለትም ድሪዎች ከጥሩ ወርቅ ሥራ፤ እንደ ተጎነጎነም ገመድ አድርግ፤ የተጎነጎኑትንም ድሪዎች በፈርጦቹ ላይ አንጠልጥል። 15ብልህ ሠራተኛም እንደሚሠራ የፍርዱን የደረት ኪስ ሥራው እንደ ኤፉዱም አሠራር ሥራው፤ ከወርቅና ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ ከጥሩ በፍታም ሥራው። 16ርዝመቱ ስንዝር ስፋቱም ስንዝር ሆኖ ትክክልና ድርብ ይሆናል። 17በአራት ተራ የሆነ የዕንቁ ፍርጥ አድርግበት፤ በፊተኛው ተራ ሰርድዮን፥ ቶጳዝዮን፥ የሚያብረቀርቅ ዕንቁ፤ 18በሁለተኛውም ተራ በሉር፥ ሰንፔር፥ አልማዝ፤ 19በሦስተኛውም ተራ ያክንት፥ ኬልቄዶን፥ አሜቴስጦኖስ፤ 20በአራተኛውም ተራ ቢረሌ፥ መረግድ፥ ኢያስጲድ በወርቅ ፈርጥ ይደረጋሉ። 21የዕንቆቹም ድንጋዮች እንደ እስራኤል ልጆች ስሞች አሥራ ሁለት ይሆናሉ፤ በየስማቸውም ማተሚያ እንደሚቀረጽ ይቀረጹ፤ ስለ አሥራ ሁለቱ ነገዶችም ይሁኑ። 22ለደረቱ ኪስም የተጎነጎኑትን ድሪዎች እንደ ገመድ አድርገህ ከጥሩ ወርቅ ሥራቸው። 23ለደረቱ ኪስም ሁለት የወርቅ ቀለበቶች ሥራ፥ ሁለቱንም ቀለበቶች በደረቱ ኪስ በሁለቱ ወገን አድርጋቸው። 24የተጎነጎኑትንም ሁለቱን የወርቅ ድሪዎች በደረቱ ኪስ ወገኖች ወዳሉት ወደ ሁለቱ ቀለበቶች ታገባቸዋለህ። 25የሁለቱንም ድሪዎች ጫፎች በሁለቱ ፈርጦች ውስጥ አግብተህ በኤፉዱ ጫንቃዎች በፊታቸው ታደርጋቸዋለህ። 26ሁለት የወርቅ ቀለበቶችም ሥራ፥ እነርሱንም በኤፉዱ ፊት ለፊት ባለው በደረቱ ኪስ በሁለቱ ጫፎች ላይ ታደርጋቸዋለህ። 27ደግሞም ሁለት የወርቅ ቀለበቶች ሥራ፥ በኤፉዱም ፊት ከጫንቃዎች በታች በብልሃት ከተጠለፈ ከኤፉዱ ቍድ በላይ በመያዣው አጠገብ ታደርጋቸዋለህ። 28የደረቱም ኪስ በብልሃት ከተጠለፈ ከኤፉዱ ቍድ በላይ እንዲሆን ከኤፉዱም እንዳይለይ፥ የደረቱን ኪስ ከቀለበቶቹ ወደ ኤፉዱ ቀለበቶች በሰማያዊ ፈትል ያስሩታል። 29አሮንም ወደ መቅደስ በገባ ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ለዘላለም መታሰቢያ የእስራኤልን ልጆች ስሞች በፍርዱ በደረት ኪስ ውስጥ በልቡ ላይ ይሸከም። 30በፍርዱ በደረት ኪስም ውስጥ ኡሪምንና ቱሚምን ታደርጋለህ፤ በእግዚአብሔርም ፊት በገባ ጊዜ በአሮን ልብ ላይ ይሆናሉ፤ አሮንም በእግዚአብሔር ፊት ሁልጊዜ የእስራኤልን ልጆች ፍርድ በልቡ ላይ ይሸከማል። 31የኤፉዱንም ቀሚስ ሁሉ ሰማያዊ አድርገው። 32ከላይም በመካከል አንገትጌ ይሁንበት፤ እንዳይቀደድም እንደ ጥሩር የተሠራ ጥልፍ በአንገትጌው ዙሪያ ይሁንበት። 33በታችኛውም ዘርፍ ዙሪያ ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ ሮማኖች አድርግ፤ በዚያም መካከል በዙሪያው የወርቅ ሻኵራዎች አድርግ፤ 34የወርቅ ሻኵራ ሮማንም፥ ሌላም የወርቅ ሻኵራ ሮማንም በቀሚሱ ዘርፍ ዙሪያውን ይሆናሉ። 35በማገልገል ጊዜም በአሮን ላይ ይሆናል፤ እርሱም እንዳይሞት ወደ መቅደሱ በእግዚአብሔር ፊት ሲገባና ሲወጣ ድምፁ ይሰማል። 36ከጥሩ ወርቅም ቅጠል የሚመስል ምልክት ሥራ፥ በእርሱም እንደ ማኅተም ቅርጽ አድርገህ፦ ቅድስና ለእግዚአብሔር የሚል ትቀርጽበታለህ። 37በሰማያዊም ፈትል በመጠምጠሚያው ፊት ላይ ታንጠለጥለዋለህ። 38በአሮንም ግምባር ላይ ይሆናል፥ አሮንም የእስራኤል ልጆች በሚያቀርቡትና በሚቀድሱት በቅዱስ ስጦታቸው ሁሉ ላይ ያለውን ኃጢአት ይሸከም፤ በእግዚአብሔርም ፊት ሞገስ እንዲሆንላቸው ቅጠል የሚመስለው ምልክቱ ሁልጊዜ በግምባሩ ላይ ይሁን። 39ሸሚዙንም ከጥሩ በፍታ ዝንጕርጕር አድርገህ፥ መጠምጠሚያውን ከበፍታ ትሠራለህ፤ በጥልፍ አሠራር መታጠቂያም ትሠራለህ። 40ለአሮንም ልጆች ሸሚዞችን መታጠቂያዎችንም ቆቦችንም ለክብርና ለጌጥ ታደርግላቸዋለህ። 41ይህንም ሁሉ ወንድምህን አሮንን ከእርሱም ጋር ልጆቹን ታለብሳቸዋለህ፤ በክህነት እንዲያገለግሉኝ ትቀባቸዋለህ፥ ትክናቸዋለህ፥ ትቀድሳቸውማለህ። 42ኀፍረተ ሥጋቸውንም ይከድኑበት ዘንድ የበፍታ ሱሪ ታደርግላቸዋለህ፤ ከወገባቸውም እስከ ጭናቸው ይደርሳል፤ 43ኃጢአትም እንዳይሆንባቸው እንዳይሞቱም፥ ወደ መገናኛው ድንኳን ሲገቡ በመቅደሱም ያገለግሉ ዘንድ ወደ መሠዊያው ሲቀርቡ በአሮንና በልጆቹ ላይ ይሆናል፤ ለእርሱ ከእርሱም በኋላ ለዘሩ ለዘላለም ሥርዓት ይሆናል።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ