የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘጸአት 24

24
1ሙሴንም፦ አንተ አሮንም ናዳብም አብዩድም ከእስራኤልም ሰባ ሽማግሌዎች ወደ እግዚአብሔር ውጡ፥ በሩቁም ስገዱ፤ 2ሙሴም ብቻውን ወደ እግዚአብሔር ይቅረብ፥ እነርሱ ግን አይቅረቡ፤ ሕዝቡም ከእርሱ ጋር አይውጡ አለው። 3ሙሴም መጣ ለሕዝቡም የእግዚአብሔርን ቃሎች ሁሉ ሥርዓቱንም ሁሉ ነገረ፤ ሕዝቡም ሁሉ በአንድ ድምፅ፦ እግዚአብሔር የተናገራቸውን ቃሎች ሁሉ እናደርጋለን ብለው መለሱ። 4ሙሴም የእግዚአብሔርን ቃሎች ጻፈ ማለዳም ተነሣ፥ ከተራራውም በታች መሠዊያን፥ አሥራ ሁለትም ሐውልቶች ለአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ሠራ። 5የሚቃጠል መሥዋዕት እንዲያቀርቡ፥ ለእግዚአብሔርም ስለ ደኅንነት መሥዋዕት በሬዎችን እንዲሠዉ የእስራኤልን ልጆች ጎበዛዝት ሰደደ። 6ሙሴም የደሙን እኵሌታ ወስዶ በቆሬ ውስጥ አደረገው፤ የደሙንም እኵሌታ በመሠዊያው ረጨው። 7የቃል ኪዳኑንም መጽሐፍ ወስዶ ለሕዝቡ አነበበላቸው፤ እነርሱም፦ እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን እንታዘዛለንም አሉ። 8ሙሴም ደሙን ውስዶ በሕዝቡ ላይ ረጨው፦ በዚህ ቃል ሁሉ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ያደረገው የቃል ኪዳኑ ደም እነሆ አለ። 9ሙሴም አሮንም ናዳብም አብዩድም ከእስራኤልም ሰባ ሽማግሌዎች ወጡ፤ 10የእስራኤልንም አምላክ አዩ፤ ከእግሩም በታች እንደ ሰማይ መልክ የሚያበራ እንደ ብሩህ ሰንፔር ድንጋይ የሚመስል ወለል ነበረ። 11እጁንም በእስራኤል አዛውንቶች ላይ አልዘረጋም፤ እነርሱም እግዚአብሔርን አዩ፥ በሉም ጠጡም። 12እግዚአብሔርም ሙሴን፦ ወደ እኔ ወደ ተራራው ውጣ፥ በዚያም ሁን፤ እነርሱን ታስተምር ዘንድ እኔ የጻፍሁትን ሕግና ትእዛዝ የድንጋይም ጽላት እሰጥሃለሁ አለው። 13ሙሴና ሎሌው ኢያሱ ተነሡ፤ ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ተራራ ወጣ። 14ሽማግሌዎችንም፦ ወደ እናንተ እስክንመለስ ድረስ በዚህ ቆዩን፤ አሮንና ሖርም እነሆ ከእናንተ ጋር ናቸው፥ ነገረተኛም ቢኖር ወደ እነርሱ ይምጣ አላቸው። 15ሙሴም ወደ ተራራ ወጣ፥ ደመናውም ተራራውን ሸፈነው። 16የእግዚአብሔርም ክብር በሲና ተራራ ላይ ተቀመጠ፥ ደመናውም ስድስት ቀን ሸፈነው፤ በሰባተኛውም ቀን ከደመናው ውስጥ ሙሴን ጠራው። 17በተራራው ራስ ላይ በእስራኤል ልጆች ፊት የእግዚአብሔር ክብር መታየት እንደሚያቃጥል እሳት ነበረ። 18ሙሴም ወደ ደመናው ውስጥ ገባ ወደ ተራራውም ወጣ፤ ሙሴም በተራራው ላይ አርባ ቀን አርባ ሌሊትም ቆየ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ