የእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ እግዚአብሔር እንዳዘዘ ከሲን ምድረ በዳ ሊጓዙ ተነሡ፥ በራፊዲምም ሰፈሩ፤ ሕዝቡም ይጠጡ ዘንድ ውኃ አልነበረም። ሕዝቡም ሙሴን ተጣሉት፦ የምንጠጣውን ውኃ ስጠን አሉት። ሙሴም፦ ለምን ትጣሉኛላችሁ? እግዚአብሔርንስ ለምን ትፈታተናላችሁ? አላቸው። ሕዝቡም በዚያ ስፍራ ውኃ ተጠሙ፦ እኛንና ልጆቻችንን ከብቶቻችንንም በጥማት ልትገድል ለምን ከግብፅ አወጣኽን? ሲሉ በሙሴ ላይ አንጎራጎሩ። ሙሴም፦ ሊወግሩኝ ቀርበዋልና በዚህ ሕዝብ ምን ላድርግ? ብሎ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ። እግዚአሔርም ሙሴን፦ በሕዝቡ ፊት እለፍ፥ ከእስራኤልም ሽማግሌዎች ከአንተ ጋር ውሰድ፤ ወንዙንም የመታህባትን በትር በእጅህ ይዘሃት ሂድ። እነሆ እኔ በዚያ በኮሬብ በዓለት ላይ በፊትህ እቆማለሁ፤ ዓለቱንም ትመታለህ፥ ሕዝቡም ይጠጣ ዘንድ ከእርሱ ውኃ ይወጣል አለው። ሙሴም በእስራኤል ሽማግሌዎች ፊት እንዲሁ አደረገ። ስለ እስራኤልም ልጆች ክርክር፦ እግዚአብሔር በመካከላችን ነውን ወይስ አይደለም? ሲሉ እግዚአብሔርን ስለተፈታተኑት የዚያን ስፍራ ስም ማሳህ፥ ደግሞም መሪባ ብሎ ጠራው።
ኦሪት ዘጸአት 17 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘጸአት 17:1-7
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos