እግዚአብሔርም ሙሴን፦ በሕጌ ይሄዱ ወይም አይሄዱ እንደሆነ እኔ እንድፈትናቸው፥ እነሆ ከሰማይ እንጀራን አዘንብላችኋለሁ፤ ሕዝቡም ወጥተው ለዕለት ለዕለት የሚበቃቸውን ይልቀሙ። እንዲህም ይሆናል፤ በስድስተኛው ቀን ያመጡትን ያዘጋጁ፥ ዕለት ዕለትም ከሚለቅሙት ይልቅ ሁለት እጥፍ ይሁን አለው። ሙሴና አሮንም ለእስራኤል ልጆች ሁሉ፦ እግዚአብሔር ከግብፅ ምድር እንዳወጣችሁ ማታ ታውቃላችሁ፥ የእግዚአብሔርንም ክብር ጥዋት ታያላችሁ፤ በእግዚአብሔር ላይ ያንጎራጎራችሁትን ሰምቶአልና በእኛም ላይ የምታንጎራጕሩ እኛ ምንድር ነን? አሉ። ሙሴም፦ እግዚአብሔር ያንጎራጎራችሁበትን ማንጎራጎራችሁን ሰምቶአልና በመሸ ጊዜ ትበሉ ዘንድ ሥጋን፥ ማልዶም ትጠግቡ ዘንድ እንጀራን እግዚአብሔር ይሰጣችኋል፤ እኛም ምንድር ነን? ማንጎራጎራችሁ በእግዚአብሔር ላይ ነው እንጂ በእኛ አይደለም አለ። ሙሴም አሮንን፦ ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ፦ ማንጎራጎራችሁን ሰምቶአልና ወደ እግዚአብሔር ፊት ቅረቡ በል አለው። እንዲህም ሆነ፤ አሮን ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ በተናገረ ጊዜ ወደ ምድረ በዳ ፊታቸውን አቀኑ፤ እነሆም የእግዚአብሔር ክብር በደመናው ታየ። እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፦ የእስራኤልን ልጆች ማንጎራጎር ሰማሁ፦ ወደ ማታ ሥጋን ትበላላችሁ፥ ማለዳም እንጀራን ትጠግባላችሁ፤ እኔም እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ በላቸው። እንዲህም ሆነ በመሸ ጊዜ ድርጭቶች መጡ፥ ሰፈሩንም ከደኑት ማለዳም በሰፈሩ ዙሪያ ጠል ወድቆ ነበር። የወደቀውም ጠል ባለፈ ጊዜ፥ እነሆ በመሬት ላይ እንደ ደቃቅ ውርጭ ሆኖ ቅርፊት የሚመስል ደቃቅ ነገር በምድረ በዳ ታየ። የእስራኤልም ልጆች ባዩት ጊዜ ያ ምን እንደ ሆነ አላወቁምና እርስ በእርሳቸው፦ ይህ ምንድር ነው? ተባባሉ። ሙሴም፦ ትበሉት ዘንድ እግዚአብሔር የሰጣችሁ እንጀራ ነው። እግዚአብሔር ያዘዘው ነገር ይህ ነው፦ እያንዳንዱ የሚበላውን ያህል ይልቀም በድኳኑ ባሉት ነፍሶች ቁጥር ለአንድ ሰው አንድ ጎሞር ውሰዱ አላቸው። የእስራኤልም ልጆች እንዲሁ አደረጉ፤ አንዱ አብዝቶ አንዱም እሳንሶ ለቀመ። በጎሞርም በሰፈሩት ጊዜ እጅግ ለለቀመ አልተረፈውም ጥቂትም ለለቀመ አልጎደለበትም፤ ሁሉ እያንዳንዱ የሚበላውን ያህል ለቀመ። ሙሴም፦ ማንም ከእርሱ አንዳች ለነገ አያስቀር አላቸው። ነገር ግን ሙሴን አልሰሙትም፤ አንዳንድ ሰዎችም ከእርሱ ለነገ አስቀሩ፥ እርሱም ተላ ሸተተም፤ ሙሴም ተቆጣቸው።
ኦሪት ዘጸአት 16 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘጸአት 16:4-20
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች