ኦሪት ዘጸአት 14:1-14

ኦሪት ዘጸአት 14:1-14 አማ54

እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ተመልሰው በሚግዶልና በባሕር መካከል፥ በበኣልዛፎንም ፊት ለፊት ባለው በፊሀሒሮት ፊት እንዲሰፍሩ ለእስራኤል ልጆች ተናገር፤ ከእርሱም አጠገብ በባህር ዳር ትሰፍራላችሁ። ፈርዖንም ስለ እስራኤል ልጆች፦ ‘በምድር ይቅበዘበዛሉ፤ ምድረ በዳም ዘጋቻቸው፤’ ይላል። እኔም የፈርዖንን ልብ አጸናለሁ፤ እርሱም ያባርራቸዋል፤ በፈርዖንና በሠራዊቱም ሁሉ ላይ ክብር አገኛለሁ፤ ግብፃውያንም እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።” እነርሱም እንዲሁ አደረጉ። ሕዝቡም እንደ ኮበለሉ ለግብፅ ንጉሥ ነገሩት፤ የፈርዖንና የባሪያዎቹም ልብ በሕዝቡ ላይ ተለወጠና፦ “እንዳይገዛልን እስራኤልን የለቀቅነው ምን አድርገናል?” አሉ። ሰረገላውንም አሰናዳ፤ ሕዝቡንም ከእርሱ ጋር ወሰደ፤ ስድስት መቶ የተመረጡ ሰረገሎችንም፥ የግብፅንም ፈረሶች ሁሉ፥ በእያንዳንዱም ሰረገላ ሁሉ ላይ ሦስተኞችን ወሰደ። እግዚአብሔርም የግብፅን ንጉሥ የፈርዖንን ልብ አጸና፤ እርሱም የእስራኤልን ልጆች አሳደደ፤ የእስራኤልም ልጆች ከፍ ባለች እጅ ወጡ። ግብፃውያንም የፈርዖን ፈረሶች ሰረገሎቹም ፈረሰኞቹም ሠራዊቱም ሁሉ፥ አሳደዱአቸው፤ በባሕሩ ዳር በበኣልዛፎን ፊት ለፊት ባለው በፊሀሒሮት አጠገብ ሰፍረው አገኙአቸው። ፈርዖንም በቀረበ ጊዜ የእስራኤል ልጆች ዐይናቸውን አነሡ፤ እነሆም ግብፃውያን በኋላቸው ገሥግሠው ነበር፤ የእስራኤልም ልጆች እጅግ ፈሩ፤ ወደ እግዚአብሔርም ጮኹ። ሙሴንም “በግብፅ መቃብር ስላልኖረ በምድረ በዳ እንሞት ዘንድ አወጣኸንን? ከግብፅ ታወጣን ዘንድ ይህ ያደረግህብን ምንድር ነው? ‘በምድረ በዳ ከምንሞት ብንገዛላቸው ይሻላልና ተወን፤ ለግብፃውያን እንገዛ’ ብለን በግብፅ ሳለን ያልንህ ቃል ይህ አይደለምን?” አሉት። ሙሴም ለሕዝቡ፦ “አትፍሩ፤ ዛሬ የምታዩአቸውን ግብፃውያንን ለዘላለም አታዩአቸውምና ቁሙ፤ ዛሬ ለእናንተ የሚያደርጋትን የእግዚአብሔርን ማዳን እዩ። እግዚአብሔር ስለ እናንተ ይዋጋል፤ እናንተም ዝም ትላላችሁ፤” አላቸው።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}