ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እስራኤላውያን ተመልሰው፥ በሚግዶልና በቀይ ባሕር መካከል ባለው ፒሃሒሮት ፊት ለፊት በባዓልጸፎን አጠገብ እንዲሰፍሩ ንገራቸው። እነሆ፥ ንጉሡ እስራኤላውያን በበረሓ ተዘግተው በአገሪቱ ዙሪያ የሚንከራተቱ ይመስለዋል። እኔም ልቡን ስለማደነድነው ያሳድዳችኋል፤ ስለዚህም በንጉሡና በሠራዊቱ ላይ የምጐናጸፈው ድል ለእኔ ክብር ይሆናል፤ በዚያን ጊዜ ግብጻውያን እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንኩ ያውቃሉ።” እስራኤላውያንም እንደ ተነገራቸው አደረጉ። የግብጽ ንጉሥ ሕዝቡ ማምለጣቸው በተነገረው ጊዜ እርሱና መኳንንቱ ሐሳባቸውን ለውጠው “ይህ ያደረግነው ነገር ምንድን ነው? እስራኤላውያን አምልጠው እንዲሄዱ ስንፈቅድ አገልጋዮቻችንን ሁሉ ማጣታችን አይደለምን?” አሉ። ንጉሡም ሠረገላውን አዘጋጅቶ ሠራዊቱን አንቀሳቀሰ። ስድስት መቶ ምርጥ ሠረገሎችን ጨምሮ በግብጽ ያሉትን ሠረገሎች ሁሉ አሰለፈ፤ የጦር አዛዦችንም መደበላቸው፤ እግዚአብሔር የንጉሡን ልብ ስላደነደነ በድፍረት በመውጣት ላይ የነበሩትን እስራኤላውያንን አሳደዳቸው፤ የግብጽ ሠራዊት በፈረሶችና በሠረገላዎች ከፈረሰኞች ጋር ሆኖ ተከታተላቸው፤ በቀይ ባሕር ፊት ለፊት ባሉት በፒሃሒሮት በባዓልጸፎን አጠገብ በሰፈሩበት ቦታ ደረሱባቸው። እስራኤላውያን ንጉሡና ሠራዊቱ በእነርሱ ላይ አደጋ ለመጣል መምጣታቸውን አይተው እጅግ ፈሩ፤ እንዲረዳቸውም ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ ሙሴንም እንዲህ አሉት፦ “ከቶ በግብጽ የመቃብር ቦታ አልነበረምን? ታዲያ በዚህ በረሓ እንድንሞት ያመጣኸን ለምንድን ነው? ከግብጽ አውጥተኸን ምን እንደ ደረሰብን እስቲ ተመልከት! ይህ ሁሉ እንደሚሆን ገና ከዚያ ሳንወጣ ነግረንህ አልነበረምን? እንዲያውም ‘እባክህ ተወን፥ ለግብጻውያን ባርያዎች ሆነን እናገልግል’ ብለንህ ነበር፤ በእርግጥም በዚህ በረሓ ከመሞት፥ በዚያ ባርያዎች ሆነን መኖር በተሻለን ነበር።” ሙሴም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “አይዞአችሁ አትፍሩ! ባላችሁበት ጸንታችሁ ቁሙ፤ እግዚአብሔር እናንተን ለማዳን የሚያደርገውን ዛሬ ታያላችሁ፤ እነዚህን ዛሬ የምታዩአቸውን ግብጻውያን ዳግመኛ አታዩአቸውም። እግዚአብሔር ስለ እናንተ ይዋጋል፤ እናንተ ማድረግ የሚገባችሁ ጸጥ ብላችሁ ሁኔታውን መጠበቅ ብቻ ነው።”
ኦሪት ዘጸአት 14 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘጸአት 14:1-14
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች