ለአስቴርም እንዲያሳያት ለመጥፋታቸው በሱሳ የተነገረውን የአዋጁን ጽሕፈት ቅጅ ሰጠው፥ ወደ ንጉሡም ገብታ ስለ ሕዝብዋ ትለምነውና ትማልደው ዘንድ እንዲነግራትና እንዲያዝዛት ነገረው። አክራትዮስም መጥቶ የመርዶክዮስን ቃል ለአስቴር ነገራት። አስቴርም አክራትዮስን ተናገረችው፥ ለመርዶክዮስም እንዲህ የሚል መልእክት ሰጠችው፦ የንጉሡ ባሪያዎችና በአገሮችም የሚኖሩ ሕዝብ ሁሉ ወንድ ወይም ሴት ቢሆን ሳይጠራ ወደ ንጉሡ ወደ ውስጠኛው ወለል የሚገባ ሁሉ፥ በሕይወት ይኖር ዘንድ ንጉሡ የወርቁን ዘንግ ካልዘረጋለት በቀር፥ እርሱ ይሞት ዘንድ ሕግ እንዳለ ያውቃሉ፥ እኔ ግን ወደ ንጉሡ ለመግባት ይህን ሠላሳውን ቀን አልተጠራሁም። አክራትዮስም የአስቴርን ቃል ለመርዶክዮስ ነገረው። መርዶክዮስም አክራትዮስን፦ ሂድና ለአስቴር እንዲህ በላት አለው፦ አንቺ፦ በንጉሥ ቤት ስለ ሆንሁ ከአይሁድ ሁሉ ይልቅ እድናለሁ ብለሽ በልብሽ አታስቢ። በዚህ ጊዜ ቸል ብትዪ ዕረፍትና መዳን ለአይሁድ ከሌላ ስፍራ ይሆንላቸዋል፥ አንቺና የአባትሽ ቤት ግን ትጠፋላችሁ፥ ደግሞስ ወደ መንግሥት የመጣሽው እንደዚህ ላለው ጊዜ እንደ ሆነ ማን ያውቃል? አስቴርም እንዲህ ብሎ ለመርዶክዮስ እንዲመልስ አዘዘችው፦ ሄደህ በሱሳ ያሉትን አይሁድ ሁሉ ሰብስብ፥ ለእኔም ጹሙ፥ ሦስት ቀን ሌሊቱንና ቀኑን አትብሉም፥ አትጠጡም፥ እኔና ደንገጥሮቼ ደግሞ እንዲሁ እንጾማለን፥ ምንም እንኳ ያለ ሕግ ቢሆን ወደ ንጉሡ እገባለሁ፥ ብጠፋም እጠፋለሁ። መርዶክዮስም ሄዶ አስቴር እንዳዘዘችው ሁሉ አደረገ።
መጽሐፈ አስቴር 4 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ አስቴር 4:8-17
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች