የአይሁድን ሕዝብ ለማስፈጀት በሱሳ ከተማ የተላለፈውን የዐዋጅ ቅጂም ለሀታክ ሰጠው፤ ይህንኑ የዐዋጅ ቅጂ ወስዶ ለአስቴር እንዲሰጣትና የሆነውንም ነገር ሁሉ እንዲገልጥላት፥ እንዲሁም ወደ ንጉሡ ዘንድ ገብታ ስለ ሕዝብዋ ምሕረትን እንድትለምን ይነግራት ዘንድ ሀታክን ለመነው። ሀታክም ይህን ሁሉ ፈጸመ፤ አስቴርም ከዚህ የሚከተለውን መልእክት ለመርዶክዮስ እንዲነግር ሀታክን መልሳ ላከችው፤ “እንደሚታወቀው ሁሉ ወንድም ሆነ ሴት፥ ማንም ሰው ሳይጠራ ወደ ውስጠኛው የቤተ መንግሥቱ አደባባይ ለመግባትና ንጉሡን ለማየት ቢሞክር በሞት ይቀጣል፤ እንግዲህ ሕጉ ይህ ሲሆን፥ ከንጉሡ አማካሪዎች እስከ ሕዝቡ ድረስ ማንም ሰው የሚያውቀው ጉዳይ ነው፤ በሕጉ መሠረት ከሞት ለመዳን የሚችለው ማንም ሰው ወደዚያ በሚገባበት ጊዜ ንጉሡ ፈቅዶ የወርቅ በትሩን ሲዘረጋለት ብቻ ነው፤ እኔ ግን ወደ ንጉሡ ለመግባት ከተጠራሁ እነሆ ሠላሳ ቀኖች አልፈውኛል።” መርዶክዮስም የአስቴርን መልእክት ከተቀበለ በኋላ፥ ከዚህ የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ላከባት፤ “አንቺ በቤተ መንግሥት ለመኖር በመቻልሽ ከሌሎች አይሁድ የተሻለ ዋስትና ያለሽ አይምሰልሽ፤ እንደዚህ ባለ ጊዜ ችላ ብለሽ ዝም ብትዪ፥ ለአይሁድ ከሌላ ቦታ ርዳታ መምጣቱ አይቀርም፤ እነርሱም በእርግጥ ይድናሉ፤ አንቺ ግን ትሞቻለሽ፤ የአባትሽም የቤተሰብ ሐረግ ተቋርጦ ይቀራል፤ ነገር ግን አንቺ ንግሥት የሆንሽው በዚህ መከራ ጊዜ እኛን ለመታደግ እንደ ሆነ ማን ያውቃል?” አስቴርም ለመርዶክዮስ እንዲህ ስትል መለሰችለት፦ “ሄደህ በሱሳ የሚገኙትን አይሁድ በአንድነት ሰብስብ፤ ጾም ዐውጃችሁም ለእኔ ጸልዩ፤ እስከ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ምንም ዐይነት ምግብ አትብሉ፤ ምንም ዐይነት መጠጥ አትጠጡ፤ እኔና ደንገጡሮቼም በዚሁ ዐይነት እንቈያለን፤ ከዚህም በኋላ በሕግ የተከለከለ ቢሆንም ደፍሬ ወደ ንጉሡ ዘንድ እገባለሁ፤ ይህን በማድረጌ ብሞትም ልሙት።” መርዶክዮስም ተነሥቶ ሄደ፤ አስቴር በነገረችውም መሠረት ሁሉን ነገር አደረገ።
መጽሐፈ አስቴር 4 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ አስቴር 4:8-17
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች