ኦሪት ዘዳግም 25:1-19

ኦሪት ዘዳግም 25:1-19 አማ54

በሰዎች መካከል ጠብ ቢሆን፥ ወደ ፍርድም ቢመጡ፥ ፈራጆችም ቢፈርዱባቸው፥ ጻድቁን፦ ደኅና ነህ፥ የበደለውንም፦ በደለኛ ነህ ይበሉአቸው። በደለኛውም መገረፍ ቢገባው እንዲገረፍ ፈራጁ በፊቱ በምድር ላይ ያጋድመው፤ የግርፋቱም ቁጥር እንደ ኃጢአቱ መጠን ይሁን። ግርፋቱም አርባ ይሁን፤ ከዚህ በላይ ጨምሮ ብዙ ግርፋት ቢገርፈው ወንድምህ በፊትህ ነውረኛ ይሆናልና ከዚህ በላይ አይጨመርበት። እህል የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር። ወንድማማቾች በአንድነት ቢቀመጡ፥ አንዱም ልጅ ሳይኖረው ቢሞት፥ የሞተው ሰው ሚስት ሌላ ሰው ታገባ ዘንድ ወደ ውጭ አትሂድ፤ ነገር ግን የባልዋ ወንድም ወደ እርስዋ ገብቶ እርስዋን ያግባ፥ ከእርስዋም ጋር ይኑር። የምዋቹ ስም ከእስራኤል ዘንድ እንዳይጠፋ ከእርስዋ የሚወለደው በኩር ልጅ በሞተው በወንድሙ ስም ይጠራ። ያም ሰው የወንድሙን ሚስት ማግባት ባይወድድ፥ ዋርሳይቱ በበሩ አደባባይ ወደሚቀመጡ ሽማግሌዎች ሄዳ፦ ዋርሳዬ በእስራኤል ዘንድ ለወንድሙ ስም ማቆም እንቢ አለ፤ ከእኔ ጋር ሊኖርም አልወደደም ትበላቸው። የከተማውም ሽማግሌዎች ጠርተው ይጠይቁት፤ እርሱም በዚያ ቆሞ፦ አገባት ዘንድ አልወድድም ቢል፥ ዋርሳይቱ በሽማግሌዎቹ ፊት ወደ እርሱ ቀርባ፦ የወንድሙን ቤት በማይሠራ ሰው ላይ እንዲህ ይደረግበታል ስትል ጭማውን ከእግሩ ታውጣ፥ በፊቱም እንትፍ ትበልበት። በእስራኤልም ዘንድ ስሙ የጫማ ፈቱ ቤት ተብሎ ይጠራ። ሁለት ሰዎች እርስ በርሳቸው ቢጣሉ፥ የአንደኛውም ሚስት ባልዋን ከሚመታው ሰው እጅ ታድነው ዘንድ ብትቀርብ፥ እጅዋንም ዘርግታ ብልቱን ብትይዝ፥ እጅዋን ቁረጥ፥ ዓይንህም አትራራላት። በከረጢትህ ውስጥ ታላቅና ታናሽ የሆነ ሁለት ዓይነት ሚዛን አይኑርልህ። በቤትህ ውስጥ ታላቅና ታናሽ የሆነ ሁለት ዓይነት መስፈሪያ አይኑርልህ። ይህን የሚያደርግ ሁሉ ክፋትንም የሚያደርግ ሁሉ በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጣላ ነውና አምላክህ እግዚአብሔር በሚሰጥህ ምድር ላይ ዕድሜህ ይረዝም ዘንድ እውነተኛና ፍጹም ሚዛን ይሁንልህ፤ እውነተኛና ፍጹም መስፈሪያም ይሁንልህ። ከግብፅ በወጣችሁ ጊዜ አማሌቅ በመንገድ ላይ ያደረገብህን አስብ፤ በመንገድ ላይ እንደ ተቃወመህ፥ አንተም ተስኖህ ደክመህም ሳለህ ከአንተ በኋላ ደክመው የነበሩትን ሁሉ እንደ መታ፤ እግዚአብሔርንም አልፈራም። ስለዚህ አምላክህ እግዚአብሔር ትወርሳት ዘንድ በሚሰጥህ ምድር ከሚከብቡህ ጠላቶችህ ሁሉ አምላክህ እግዚአብሔር ባሳረፈህ ጊዜ፥ የአማሌቅን ዝክረ ስሙን ከሰማይ በታች አጥፋው፤ ይህንን አትርሳ።