በሰዎች መካከል ጠብ ቢነሣና ወደ ፍርድ አደባባይ ቢሄዱ፣ ዳኞች ተበዳይን ነጻ፣ በዳይን ግን ጥፋተኛ በማድረግ የፍርድ ውሳኔ ይስጡ። በደለኛው ሰው መገረፍ የሚገባው ሆኖ ከተገኘ፣ ዳኛው መሬት ላይ ያጋድመው፤ ለጥፋቱ ተመጣጣኝ የሆነ ግርፋት እርሱ ባለበት ይገረፍ። ሆኖም ግርፋቱ ከአርባ የሚበልጥ አይሁን፤ ከዚህ ካለፈ ግን፣ ወንድምህ በፊትህ የተዋረደ ይሆናል። የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር። ወንድማማቾች በአንድነት ቢኖሩና ከእነርሱ አንዱ ወንድ ልጅ ሳይወልድ ቢሞት፣ የሟቹ ሚስት ከቤተ ሰቡ ውጭ ባል ማግባት የለባትም። የባሏ ወንድም ይውሰዳትና ያግባት፤ የዋርሳነት ግዴታውንም ይፈጽምላት። በመጀመሪያ የምትወልደውም ልጅ ስሙ ከእስራኤል ፈጽሞ እንዳይጠፋ በሟች ወንድሙ ስም ይጠራ። ሆኖም ግን አንድ ሰው የወንድሙን ሚስት ለማግባት ባይፈልግ፣ ሴትዮዋ በከተማዪቱ በር ወዳሉት ሽማግሌዎች ሄዳ፣ “የባለቤቴ ወንድም የወንድሙን ስም በእስራኤል ለማስጠራት አልፈለገም፤ የዋርሳነት ግዴታውንም አልፈጸመልኝም” ትበላቸው። ከዚያም የከተማው ሽማግሌዎች ያን ሰው ጠርተው ያነጋግሩት፤ እርሱም፣ “እርሷን ላገባት አልፈልግም” ብሎ በሐሳቡ ቢጸና፣ የወንድሙም ሚስት በሽማግሌዎች ፊት ወደ እርሱ ቀርባ፣ የአንድ እግሩን ጫማ በማውለቅ በፊቱ ላይ ትትፋበትና “የወንድሙን ቤት በማይሠራ ሰው ላይ እንዲህ ያለው ድርጊት ይፈጸምበታል” ትበል። የዚያም ሰው የዘር ሐረግ በእስራኤል ዘንድ፣ “ጫማው የወለቀበት ቤት” ተብሎ ይታወቃል። ሁለት ሰዎች ቢደባደቡ፣ የአንደኛው ሚስት ባሏን ከደብዳቢው እጅ ለማስጣል መጥታ፣ እጇን ዘርግታ ብልቱን ብትይዘው፣ እጇን ቍረጠው፤ አትራራላት። በከረጢትህ ውስጥ ከባድና ቀላል የሆኑ ሁለት የተለያዩ ሚዛኖች አይኑሩህ። በቤትህም ውስጥ ትልቅና ትንሽ የሆኑ ሁለት የተለያዩ መስፈሪያዎች አይኑሩህ። አምላክህ እግዚአብሔር በሚሰጥህ ምድር ዕድሜህ እንዲረዝም፣ ጻድቅና የታመነ ሚዛንና መስፈሪያ ይኑርህ። አምላክህ እግዚአብሔር እንዲህ ያሉትን ነገሮች የሚፈጽመውንና የሚያምታታውን ሁሉ ይጸየፈዋልና። ከግብጽ በወጣህ ጊዜ፣ አማሌቅ በመንገድ በአንተ ላይ ያደረገብህን አስታውስ፤ ደክመህና ዝለህ በነበርህበት ጊዜ፣ በጕዞ ላይ አግኝተውህ፣ ከኋላ ያዘግሙ የነበሩትን ሁሉ ገደሉ፤ እግዚአብሔርንም አልፈሩም። አምላክህ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር ዙሪያ ካሉት ጠላቶችህ ሁሉ ባሳረፈህ ጊዜ፣ ከሰማይ በታች ያለውን የአማሌቅን መታሰቢያ ደምስስ፤ ከቶ እንዳትረሳ!
ዘዳግም 25 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘዳግም 25
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘዳግም 25:1-19
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos