ኦሪት ዘዳግም 11
11
1እንግዲህ አምላክህን እግዚአብሔርን ውደድ፥ ሕጉንም ሥርዓቱንም ፍርዱንም ትእዛዙንም ሁልጊዜ ጠብቅ። 2የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ተግሣጽ፥ ታላቅነቱንም፥ የጸናችም እጁን፥ የተዘረጋውንም ክንዱን፥ 3በግብፅም መካከል በንጉሡ በፈርዖንና በአገሩ ሁሉ ላይ ያደረጋትን ተአምራቱንና ሥራውን፥ 4በተከተሉአችሁም ጊዜ በኤርትራ ባሕር ውኃ እንዳሰጠማቸው፥ እግዚአብሔርም እስከ ዛሬ ድረስ እንዳጠፋቸው፥ በግብፅ ጭፍራ በፈረሶቻቸውም በሰረገሎቻቸውም ያደረገውን፥ 5ወደዚህ ስፍራ እስክትመጡ ድረስ በምድረ በዳ ያደረገላችሁን፥ 6በእስራኤልም ሁሉ መካከል ምድር አፍዋን ከፍታ እነርሱንና ቤተሰቦቻቸውን ድንኳኖቻቸውንም ለእነርሱም የነበራቸውን ሁሉ በዋጠቻቸው በሮቤል ልጅ በኤልያብ ልጆች በዳታንና በአቤሮን ያደረገውን ላላወቁትና ላላዩት ልጆቻችሁ አልነግራቸውምና እናንተ ዛሬ እወቁ። 7ነገር ግን እግዚአብሔር ያደረጋትን ታላቂቱን ሥራ ሁሉ ዓይኖቻችሁ አይተዋል። 8-9እንግዲህ እንድትጠነክሩ፥ ትወርሱአትም ዘንድ ወደምትሻገሩባት ምድር እንድትገቡ እንድትወርሱአትም፥ እግዚአብሔርም ለእነርሱና ለዘራቸው ይሰጣት ዘንድ በማለላቸው ወተትና ማርም በምታፈስሰው ምድር ዕድሜአችሁ እንዲረዝም፥ ዛሬ ለእናንተ የማዝዘውን ትእዛዝ ሁሉ ጠብቁ። 10ትወርሳት ዘንድ የምትገባባት ምድር፥ በአትክልት ስፍራ እንደሚዘሩ ዘርህን እንደዘራህባት፥ በእግርህም እንዳጠጣሃት፥ እንደ ወጣህባት እንደ ግብፅ ምድር አይደለችም። 11ነገር ግን ትወርሱአት ዘንድ ተሻግራችሁ የምትገቡባት ምድር ኮረብታና ሸለቆ ያለባት አገር ናት፤ በሰማይ ዝናብ ውኃ ትረካለች። 12አምላክህ እግዚአብሔር የሚጎበኛት አገር ናት፤ ከዓመቱ መጀመሪያ እስከ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ የአምላክህ የእግዚአብሔር ዓይን ሁልጊዜ በእርስዋ ላይ ነው። 13እንዲህም ይሆናል፤ እናንተ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ትወድዱ ዘንድ፥ በፍጹምም ልባችሁ በፍጹምም ነፍሳችሁ ታመልኩት ዘንድ ዛሬ ለእናንተ የማዝዘውን ትእዛዜን ፈጽማችሁ ብትሰሙ፥ 14እህልህን ወይንህንም ዘይትህንም ትሰበስብ ዘንድ በየጊዜው የበልጉን ዝናብና የክረምቱን ዝናብ ለምድራችሁ አወርዳለሁ። 15በሜዳ ለእንስሶችህ ሣርን እሰጣለሁ፥ ትበላማለህ፥ ትጠግብማለህ። 16ልባችሁ እንዳይስት፥ ፈቀቅ እንዳትሉ፥ ሌሎችንም አማልክት እንዳታመልኩ፥ እንዳትሰግዱላቸውም፥ 17የእግዚአብሔርም ቁጣ እንዳይነድድባችሁ፥ ዝናብም እንዳይዘንብ ምድሪቱም ፍሬዋን እንዳትሰጥ ሰማይን እንዳይዘጋባችሁ፤ እግዚአብሔርም ከሚሰጣችሁ ከመልካሚቱ ምድር ፈጥናችሁ እንዳትጠፉ ተጠንቀቁ። 18እንግዲህ እነዚህን ቃሎች በልባችሁና በነፍሳችሁ አኑሩ፤ እነርሱንም ለምልክት በእጃችሁ ላይ እሰሩአቸው፥ በዓይኖቻችሁም መካከል እንደክታብ ይሁኑ። 19ልጆቻችሁንም አስተምሩአቸው፥ በቤትህም ስትቀመጥ፥ በመንገድም ስትሄድ፥ ስትተኛም ስትነሣም አጫውቱአቸው። 20-21እርስዋንም እንዲሰጣቸው እግዚአብሔር ለአባቶቻችሁ በማለላቸው ምድር፥ እንደ ሰማይ ዘመን በምድር ላይ፥ ዘመናችሁ የልጆቻችሁም ዘመን ይረዝም ዘንድ በቤትህ መቃኖችና በደጃፍህም በሮች ላይ ጻፈው። 22አምላካችሁን እግዚአብሔርን ትወድዱ ዘንድ፥ በመንገዱም ሁሉ ትሄዱ ዘንድ፥ ከእርሱም ጋር ትጣበቁ ዘንድ፥ ዛሬ ለእናንተ የማዝዘውን ትእዛዝ ሁሉ ብትጠብቁ ብታደርጉአትም፥ 23እግዚአብሔር እነዚህን አሕዛብ ሁሉ ከፊታችሁ ያወጣል፥ ከእናንተም የሚበልጡትን የሚበረቱትንም አሕዛብ ትወርሳላችሁ። 24የእግራችሁ ጫማ የምትረግጣት ስፍራ ሁሉ ለእናንተ ትሆናለች፤ ከምድረ በዳም ከሊባኖስም ከታላቁም ከኤፍራጥስ ወንዝ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ባሕር ድረስ ዳርቻችሁ ይሆናል። 25በእናንተም ፊት ማንም መቆም አይችልም፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር፥ እርሱ እንደ ተናገራችሁ፥ ማስፈራታችሁን ማስደንገጣችሁንም በምትረግጡአት ምድር ሁሉ ላይ ያኖራል። 26እነሆ፥ እኔ ዛሬ በፊታችሁ በረከትንና መርገምን አኖራለሁ፤ 27በረከትም፥ እኔ ዛሬ ለእናንተ የማዝዘውን የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ብትሰሙ፤ 28መርገምም፥ የአምላካችሁን የእግዚአብሕርን ትእዛዝ ባትሰሙ፥ ዛሬ ካዘዝኋችሁ መንገድ ፈቀቅ ብትሉ፥ ሌሎችንም የማታውቍቸውን አማልክት ብትከተሉ ነው። 29አምላክህም እግዚአብሔር ትወርሳት ዘንድ አንተን ወደምትሄድባት ምድር ባገባህ ጊዜ፥ በረከቱን በገሪዛን ተራራ መርገሙንም በጌባል ተራራ ታኖራለህ። 30እነርሱም በዮርዳኖስ ማዶ፥ ከፀሐይ መግቢያ ካለችው መንገድ በኋላ፥ በዓረባ በተቀመጡት በከነዓናውያን ምድር፥ በጌልገላ ፊት ለፊት በሞሬ የአድባር ዛፍ አጠገብ ናቸው። 31አምላካችሁ እግዚአብሔር የሚሰጣችሁን ምድር ትወርሱ ዘንድ ዮርዳኖስን ትሻገራላችሁ፥ ትወርሱአታላችሁም፥ ትቀመጡባታላችሁም። 32እኔም ዛሬ በፊታችሁ የማኖራትን ሥርዓትና ፍርድ ሁሉ ታደርጉ ዘንድ ጠብቁ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘዳግም 11: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ