የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘዳግም 10

10
1በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር፦ እንደ ፊተኞች ያሉትን ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ጠርበህ ወደ እኔ ወደ ተራራው ውጣ፥ ለአንተም የእንጨት ታቦት ሥራ፤ 2በሰበርሃቸውም በፊተኞቹ ጽላቶች የነበሩትን ቃሎች በእነዚህ ጽላቶች እጽፋለሁ፥ በታቦቱም ውስጥ ታደርጋቸዋለህ አለኝ። 3ከግራርም እንጨት ታቦትን ሠራሁ፥ እንደ ፊተኞችም ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ጠረብሁ፤ ሁለቱንም ጽላቶች በእጄ ይዤ ወደ ተራራው ወጣሁ። 4ስብሰባ ተደርጎ በነበረበትም ቀን እግዚአብሔር በተራራው ላይ በእሳት ውስጥ ሆኖ የተናገራችሁን አሠርቱን ቃላት ቀድሞ ተጽፈው እንደ ነበረ በጽላቶቹ ላይ ጻፈ፤ እግዚአብሔርም እነርሱን ለእኔ ሰጠኝ። 5ተመልሼም ከተራራው ወረድሁ፥ ጽላቶችንም በሠራሁት ታቦት ውስጥ አደረግኋቸው፤ እግዚአብሔርም እንዳዘዘኝ በዚያ ኖሩ። 6የእስራኤልም ልጆች ከብኤሮት ብኔያዕቃን ወደ ሞሴራ ተጓዙ፤ በዚያም አሮን ሞተ በዚያም ተቀበረ፤ በእርሱም ፋንታ ልጁ አልዓዛር ካህን ሆነ። 7ከዚያም ወደ ጉድጎዳ ተጓዙ፤ ከጉድጎዳም ወደ ውኃ ፈሳሾች ምድር ወደ ዮጥባታ ተጓዙ። 8በዚያን ጊዜ የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ይሸከም ዘንድ፥ እርሱንም ለማገልገል በእግዚአብሔር ፊት ይቆም ዘንድ፥ በስሙም ይባርክ ዘንድ እግዚአብሔር እስከ ዛሬ ድረስ የሌዊን ነገድ ለየ። 9ስለዚህ ለሌዊ ከወንድሞቹ ጋር ክፍልና ርስት የለውም፤ አምላክህ እግዚአብሔር እንደ ተናገረው እግዚአብሔር ርስቱ ነው። 10እኔም እንደ ፊተኛው ጊዜ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በተራራው ላይ ተቀመጥሁ፤ እግዚአብሔርም በዚህ ጊዜ ደግሞ ሰማኝ፤ እግዚአብሔር ሊያጠፋህ አልወደደም። 11እግዚአብሔርም፦ ተነሥተህ በሕዝቡ ፊት ተጓዝ፤ ለአባቶቻቸውም ልሰጣቸው ወደ ማልሁላቸው ምድር ይግቡ ይውረሱአትም አለኝ። 12-13እስራኤል ሆይ፥ አሁንስ አምላክህን እግዚአብሔርን ትፈራ ዘንድ፥ በመንገዱም ሁሉ ትሄድ ዘንድ፥ አምላክህንም እግዚአብሔርን ትወድድ ዘንድ፥ በፍጹምም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ ታመልከው ዘንድ፥ መልካምም እንዲሆንልህ ዛሬ ለአንተ የማዝዘውን የእግዚአብሔርን ትእዛዝና ሥርዓት ትጠብቅ ዘንድ ነው እንጂ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ የሚፈልገው ምንድር ነው? 14እነሆ፥ ሰማይ ሰማየ ሰማያትም፥ ምድርም በእርስዋም ያለው ሁሉ የአምላክህ የእግዚአብሔር ነው። 15ብቻ እግዚአብሔር ስለ አባቶችህ ደስ ብሎታል፥ እነርሱንም ወድዶአል፤ ከእነርሱም በኋላ እናንተን ዘራቸውን እንደ ዛሬው ሁሉ ከአሕዛብ ሁሉ መካከል መረጠ። 16-17እንግዲህ አምላካችሁ እግዚአብሔር የአማልክት አምላክ የጌቶችም ጌታ፥ ታላቅ አምላክ ኃያልም የሚያስፈራም፥ በፍርድ የማያደላ፥ መማለጃም የማይቀበል ነውና እናንተ የልባችሁን ሸለፈት ግረዙ፥ ከእንግዲህ ወዲህም አንገተ ደንዳና አትሁኑ። 18ለድሃ አደጉና ለመበለቲቱ ይፈርዳል፥ መብልና ልብስም ይሰጠው ዘንድ ስደተኛውን ይወድዳል። 19እናንተ በግብፅ አገር ስደተኞች ነበራችሁና ስለዚህ ስደተኛውን ውደዱ። 20አምላክህን እግዚአብሔርን ፍራ፥ እርሱንም አምልክ፤ ከእርሱም ተጣበቅ፥ በስሙም ማል። 21ዓይኖችህ ያዩትን እነዚህን ታላላቆች የሚያስፈሩትንም ነገሮች ያደረገልህ እርሱ ክብርህ ነው፥ እርሱም አምላክህ ነው። 22አባቶችህ ሰባ ነፍስ ሆነው ወደ ግብፅ ወረዱ፤ አሁንም አምላክህ እግዚአብሔር ብዛትህን እንደ ሰማይ ከዋክብት አደረገ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ