ትንቢተ ዳንኤል 9:20-27

ትንቢተ ዳንኤል 9:20-27 አማ54

እኔም ገና ስናገርና ስጸልይ፥ በኃጢአቴና በሕዝቤም በእስራኤል ኃጢአት ስናዘዝ፥ በአምላኬም በእግዚአብሔር ፊት ስለ ተቀደሰው ስለ አምላኬ ተራራ ስለምን፥ ገናም በጸሎት ስናገር አስቀድሜ በራእይ አይቼው የነበረው ሰው ገብርኤል እነሆ እየበረረ መጣ፥ በማታም መሥዋዕት ጊዜ ዳሰሰኝ። አስተማረኝም፥ ተናገረኝም እንዲህም አለ፦ ዳንኤል ሆይ፥ ጥበብንና ማስተዋልን እሰጥህ ዘንድ አሁን መጥቻለሁ። አንተ እጅግ የተወደድህ ነህና በልመናህ መጀመሪያ ላይ ትእዛዝ ወጥቶአል፥ እኔም እነግርህ ዘንድ መጥቻለሁ፥ አሁንም ነገሩን መርምር፥ ራእዩንም አስተውል። ዓመፃን ይጨርስ፥ ኃጢአትንም ይፈጽም፥ በደልንም ያስተሰርይ፥ የዘላለምን ጽድቅ ያግባ፥ ራእይንና ትንቢትን ያትም፥ ቅዱሰ ቅዱሳኑንም ይቀባ ዘንድ በሕዝብህና በቅድስት ከተማህ ላይ ሰባ ሱባዔ ተቀጥሮአል። ስለዚህ እወቅ አስተውልም፥ ኢየሩሳሌምን መጠገንና መሥራት ትእዛዙ ከሚወጣበት ጀምሮ እስከ አለቃው እስከ መሢሕ ድረስ ሰባት ሱባዔና ስድሳ ሁለት ሱባዔ ይሆናል፥ እርስዋም በጭንቀት ዘመን ከጎዳናና ከቅጥር ጋር ትሠራለች። ከስድሳ ሁለት ጊዜ ሰባትም በኋላ መሢሕ ይገደላል፥ በእርሱም ዘንድ ምንም የለም፥ የሚመጣውም አለቃ ሕዝብ ከተማይቱንና መቅደሱን ያጠፋሉ፥ ፍጻሜውም በጐርፍ ይሆናል፥ እስከ መጨረሻም ድረስ ጦርነት ይሆናል፥ ጥፋትም ተቀጥሮአል። እርሱም ከብዙ ሰዎች ጋር ጽኑ ቃል ኪዳን ለአንድ ሱባዔ ያደርጋል፥ በሱባዔውም እኵሌታ መሥዋዕቱንና ቍርባኑን ያስቀራል፥ በርኵሰትም ጫፍ ላይ አጥፊው ይመጣል፥ እስከ ተቈረጠውም ፍጻሜ ድረስ መቅሠፍት በአጥፊው ላይ ይፈስሳል።