ትንቢተ ዳንኤል 9:20-27

ትንቢተ ዳንኤል 9:20-27 አማ05

የራሴንና የወገኖቼን የእስራኤላውያንን ኃጢአት እየተናዘዝኩ፥ ስለ ቅዱስ ተራራው በአምላኬ በእግዚአብሔር ፊት ጸሎቴን ቀጠልኩ። በዚህም ጸሎት ላይ ሳለሁ በመጀመሪያው ራእይ ያየሁት ገብርኤል እኔ ወዳለሁበት ስፍራ በፍጥነት እየበረረ መጣ፤ ጊዜውም የሠርክ መሥዋዕት የሚቀርብበት ወቅት ነበር። እርሱም እንዲህ ሲል አስረዳኝ፦ “ዳንኤል ሆይ! እኔ ወደዚህ የመጣሁት የትንቢቱን ምሥጢር እንድታውቅ ጥበብንና ማስተዋልን ልሰጥህ ነው፤ ገና መጸለይ ስትጀምር እግዚአብሔር ልመናህን ሰምቶአል፤ አንተ በእርሱ ዘንድ የተወደድክ ስለ ሆነ የጸሎትህን መልስ ልነግርህ መጥቼአለሁ፤ እንግዲህ የምነግርህን አዳምጠህ የራእዩን ትርጒም ተረዳ። “ሰባት ጊዜ ሰባ ሳምንት የተባለው እግዚአብሔር ሕዝብህንና የተቀደሰ ከተማህን ከኃጢአትና ከክፋት ነጻ ለማውጣት ውሳኔ ያደረገበት ጊዜ ነው፤ በዚያን ጊዜ በደል ይሰረያል፤ ዘለዓለማዊ ፍትሕ ይሰፍናል፤ ራእይና ትንቢት ይፈጸማል፤ ቤተ መቅደሱም ይታደሳል። ይህን ልብ ብለህ አስተውል፤ ኢየሩሳሌም እንድትታደስ ትእዛዝ ከወጣበት ጊዜ አንሥቶ መሲሕ እስከሚመጣበት ጊዜ ድረስ ሰባት ሳምንቶች ያልፋሉ፤ እንዲሁም ለሥልሳ ሁለት ሳምንት በችግር ጊዜ ኢየሩሳሌም፥ መንገዶችዋና የመከላከያ ጒድጓድዋ ይገነባሉ። ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ የመከራ ዘመን ይሆናል። ከስድሳ ሁለት ሳምንት በኋላ መሲሑ ያለ ፍትሕ ይገደላል፤ የሚገደለውም ለራሱ አይደለም፤ የሚመጣው መሪ ወታደሮች ቤተ መቅደሱንና ከተማይቱን ይደመስሳሉ፤ መጨረሻውም እንደ ጐርፍ ይመጣል፤ ውድመት ስለ ታወጀ ጦርነት እስከ መጨረሻ ይቀጥላል። ያም መሪ ለአንድ ሳምንት ከብዙ ሕዝቦች ጋር የጠበቀ ቃል ኪዳን ያደርጋል፤ በሳምንቱም እኩሌታ መሥዋዕቱንና ቊርባኑን ያስቀራል፤ በእነርሱም ፈንታ ጥፋት የሚያስከትለው ርኲሰት እንዲተካ ያደርጋል። ይህም የሚሆነው በዚያ አጥፊ መሪ ላይ የታወጀው ቅጣት እስኪፈጸም ድረስ ነው።”