በባቢሎን ንጉሥ በብልጣሶር በመጀመሪያው ዓመት ዳንኤል በአልጋው ላይ ሕልምንና የራሱን ራእይ አየ፥ ከዚያም በኋላ ሕልሙን ጻፈ፥ ዋነኛውንም ነገር ተናገረ። ዳንኤልም ተናገረ እንዲህም አለ፦ በሌሊት በራእይ አየሁ፥ እነሆም፥ አራቱ የሰማይ ነፋሳት በታላቁ ባሕር ላይ ይጋጩ ነበር። አራትን ታላላቅ አራዊት ከባሕር ወጡ፥ እያንዳንዲቱም ልዩ ልዩ ነበረች። መጀመሪያይቱ አንበሳ ትመስል ነበር፥ የንስርም ክንፍ ነበራት፥ ክንፎችዋም ከእርስዋ እስኪነቀሉ ድረስ አይ ነበር፥ ከምድርም ከፍ ከፍ ተደረገች፥ እንደ ሰውም በሁለት እግር እንድትቆም ተደረገች፥ የሰውም ልብ ተሰጣት። እነሆም፥ ሁለተኛይቱ ድብ የምትመስል ሌላ አውሬ ነበረች፥ በአንድ ወገንም ቆመች፥ ሦስትም የጐድን አጥንቶች በአፍዋ ውስጥ በጥርስዋ መካከል ነበሩ፥ እንደዚህም፦ ተነሥተሽ እጅግ ሥጋ ብዪ ተባለላት። ከዚህም በኋላ፥ እነሆ፥ ነብር የምትመስል በጀርባዋም ላይ አራት የወፍ ክንፎች የነበሩአት ሌላ አውሬ አየሁ፥ ለአውሬይቱም አራት ራሶች ነበሩአት፥ ግዛትም ተሰጣት። ከዚህም በኋላ በሌሊት ራእይ አየሁ፥ እነሆም፥ የምታስፈራና የምታስደነግጥ እጅግም የበረታች፥ ታላላቅም የብረት ጥርሶች የነበሩአት አራተኛ አውሬ ነበረች፥ ትበላና ታደቅቅ ነበር፥ የቀረውንም በእግርዋ ትረግጥ ነበር፥ ከእርስዋም በፊት ከነበሩት አራዊት ሁሉ የተለየች ነበረች፥ አሥር ቀንዶችም ነበሩአት። ቀንዶችንም ተመለከትሁ፥ እነሆም፥ በመካከላቸው ሌላ ትንሽ ቀንድ ወጣ፥ በፊቱም ከቀደሙት ቀንዶች ሦስት ተነቃቀሉ፥ እነሆም፥ በዚያ ቀንድ እንደ ሰው ዓይኖች የነበሩ ዓይኖች በትዕቢትም የሚናገር አፍ ነበሩበት። ዙፋኖችም እስኪዘረጉ ድረስ አየሁ፥ በዘመናት የሸመገለውም ተቀመጠ፥ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ፥ የራሱም ጠጕር እንደ ጥሩ ጥጥ ነበረ፥ ዙፋኑም የእሳት ነበልባል ነበረ፥ መንኰራኵሮቹም የሚነድድ እሳት ነበሩ። የእሳትም ፈሳሽ ከፊቱ ይፈልቅና ይወጣ ነበር፥ ሺህ ጊዜ ሺህ ያገለግሉት ነበር፥ እልፍ አእላፋትም በፊቱ ቆመው ነበር፥ ፍርድም ሆነ፥ መጻሕፍትም ተገለጡ። የዚያን ጊዜም ቀንዱ ይናገረው ከነበረው ከታላቁ ቃል ድምፅ የተነሣ አየሁ፥ አውሬይቱም እስክትገደል፥ አካልዋም እስኪጠፋ ድረስ፥ በእሳትም ለመቃጠል እስክትሰጥ ድረስ አየሁ። ከቀሩትም አራዊት ግዛታቸው ተወሰደ፥ የሕይወታቸው ዕድሜ ግን እስከ ዘመንና እስከ ጊዜ ድረስ ረዘመ። በሌሊት ራእይ አየሁ፥ እነሆም፥ የሰው ልጅ የሚመስል ከሰማይ ደመናት ጋር መጣ በዘመናት ወደ ሸመገለውም ደረሰ፥ ወደ ፊቱም አቀረቡት። ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ሁሉ ይገዙለት ዘንድ ግዛትና ክብር መንግሥትም ተሰጠው፥ ግዛቱም የማያልፍ የዘላለም ግዛት ነው፥ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው።
ትንቢተ ዳንኤል 7 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ ዳንኤል 7:1-14
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች