ዳንኤል 7:1-14

ዳንኤል 7:1-14 NASV

የባቢሎን ንጉሥ ቤልሻዛር በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት ዳንኤል በዐልጋው ላይ ተኝቶ ሳለ ሕልም ዐለመ፤ ራእይም አየ፤ የሕልሙንም ዋና ሐሳብ ጻፈው። ዳንኤል እንዲህ አለ፤ “አራቱ የሰማይ ነፋሳት ታላቁን ባሕር ሲያናውጡት ሌሊት በራእይ አየሁ። እርስ በርሳቸው የማይመሳሰሉ አራት ታላላቅ አራዊት ከባሕሩ ወጡ። “የመጀመሪያው፣ አንበሳ ይመስል ነበር፤ የንስርም ክንፎች ነበሩት፤ ክንፎቹ እስኪነቃቀሉ ድረስ ተመለከትሁ፤ እንደ ሰው በሁለት እግሩ እንዲቆም ከምድር ከፍ ከፍ ተደረገ፤ የሰውም ልብ ተሰጠው። “እነሆም፤ ሁለተኛው አውሬ ድብ ይመስል ነበር፤ በአንድ ጐኑ ከፍ ብሏል፤ በአፉ ውስጥ በጥርሶቹ መካከል ሦስት የጐድን ዐጥንቶች ነበሩት። እርሱም፤ ‘ተነሥ፤ እስክትጠግብ ድረስ ሥጋ ብላ!’ ተባለ። “ከዚያ በኋላ ተመለከትሁ፤ በፊቴ ነብር የሚመስል ሌላ አውሬ ነበር፤ በጀርባውም በኩል የወፍ ክንፍ የሚመስሉ አራት ክንፎች ነበሩት፤ ይህ አውሬ አራት ራስ ነበረው፤ ለመግዛትም ሥልጣን ተሰጠው። “ከዚህ በኋላ በሌሊት ራእይ አየሁ፤ በፊቴም የሚያስፈራና የሚያስደነግጥ በጣም ኀይለኛ የሆነ አራተኛ አውሬ ነበር፤ ትልልቅ የብረት ጥርሶች ነበሩት፤ ያደቅቅና ይበላ፣ የቀረውንም ሁሉ በእግሮቹ ይረጋግጥ ነበር። ከርሱ በፊት ከነበሩት አራዊት ሁሉ የተለየ ሲሆን፣ ዐሥር ቀንዶች ነበሩት። “ስለ ቀንዶቹ ሳስብ ሳለሁ፣ ከመካከላቸው አንድ ሌላ ትንሽ ቀንድ ብቅ ሲል አየሁ፤ ከመጀመሪያዎቹ ቀንዶች ሦስቱ ከፊቱ ተነቃቀሉ፤ ይህም ቀንድ የሰው ዐይኖችን የሚመስሉ ዐይኖች፣ በትዕቢትም የሚናገር አፍ ነበረው። “እኔም ስመለከት፣ “ዙፋኖች ተዘረጉ፤ ጥንታዌ ጥንቱም ተቀመጠ፤ ልብሱ እንደ በረዶ ነጭ ነበረ፤ የራሱም ጠጕር እንደ ጥጥ ነጭ ነበረ፤ ዙፋኑ የእሳት ነበልባል፣ መንኰራኵሮቹም ሁሉ እንደሚነድድ እሳት ነበሩ። የእሳት ወንዝ፣ ከፊት ለፊቱ ፈልቆ ይፈስስ ነበር፤ ሺሕ ጊዜ ሺሖች ያገለግሉት ነበር፤ እልፍ ጊዜ እልፍ በፊቱ ቆመዋል፤ የፍርድ ጉባኤ ተሰየመ፤ መጻሕፍትም ተከፈቱ። “ቀንዱም ከሚናገረው የትዕቢት ቃል የተነሣ፣ መመልከቴን ቀጠልሁ፤ አውሬው እስኪታረድና አካሉ ደቅቆ ወደሚንበለበለው እሳት እስኪጣል ድረስ ማየቴን አላቋረጥሁም። ሌሎቹም አራዊት ሥልጣናቸው ተገፍፎ ነበር፤ ነገር ግን ለተወሰነ ጊዜና ወቅት በሕይወት እንዲኖሩ ተፈቀደላቸው። “ሌሊት ባየሁት ራእይ፣ የሰውን ልጅ የሚመስል በሰማይ ደመና ጋራ ሲመጣ አየሁ፤ ወደ ጥንታዌ ጥንቱ መጣ፤ ወደ ፊቱም አቀረቡት። ሥልጣን፣ ክብርና ታላቅ ኀይል ተሰጠው፤ በልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች፣ መንግሥታትና ሕዝቦች ሰገዱለት፤ ግዛቱም ለዘላለም የማያልፍ ነው፤ መንግሥቱም ፈጽሞ የማይጠፋ ነው።