በዚያን ጊዜም ከለዳውያን ቀርበው አይሁድን ከሰሱ። ለንጉሡም ለናቡከደነፆር ተናገሩ እንዲህም አሉ፦ ንጉሥ ሆይ፥ ሺህ ዓመት ንገሥ። አንተ፥ ንጉሥ ሆይ፦ የመለከትንና የእንቢልታን፥ የመሰንቆንና የክራርን፥ የበገናንና የዋሽንትን፥ የዘፈንንም ሁሉ ድምፅ የሚሰማ ሰው ሁሉ ተደፍቶ ለወርቁ ምስል ይስገድ፥ ተደፍቶም የማይሰግድ በሚነድድ እሳት እቶን ውስጥ ይጣላል ብለህ አዘዝህ። በባቢሎን አውራጃ ሥራ ላይ የሾምሃቸው ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም የሚባሉ አይሁድ አሉ፥ ንጉሥ ሆይ፥ እነዚህ ሰዎች ትእዛዝህን እንቢ ብለዋል፥ አማልክትህን አያመልኩም፥ ላቆምኸውም ለወርቁ ምስል አይሰግዱም። ናቡከደነፆርም በብስጭትና በቍጣ ሲድራቅንና ሚሳቅን አብደናጎንም ያመጡ ዘንድ አዘዘ፥ እነዚህንም ሰዎች ወደ ንጉሡ ፊት አመጡአቸው። ናቡከደነፆርም፦ ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም ሆይ፥ አምላኬን አለማምለካችሁ፥ ላቆምሁትም ለወርቁ ምስል አለመስገዳችሁ እውነት ነውን? አሁንም የመለከቱንና የእንቢልታውን የመሰንቆውንና የክራሩን የበገናውንና የዋሽንቱን የዘፈኑንም ሁሉ ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ ተደፍታችሁ ላሠራሁት ምስል ብትሰግዱ መልካም ነው፥ ባትሰግዱ ግን በዚያ ጊዜ በሚነድድ እሳት እቶን ውስጥ ትጣላላችሁ፥ ከእጄስ የሚያድናችሁ አምላክ ማን ነው? ብሎ ተናገራቸው። ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም መለሱ ንጉሡንም፦ ናብከደነፆር ሆይ፥ በዚህ ነገር እንመልስልህ ዘንድ አስፈላጊያችን አይደለም። የምናመልከው አምላካችን ከሚነድደው ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል፥ ከእጅህም ያድነናል፥ ንጉሥ ሆይ! ነገር ግን፥ ንጉሥ ሆይ፥ እርሱ ባያድነን፥ አማልክትህን እንዳናመልክ ላቆምኸውም ለወርቁ ምስል እንዳንሰግድለት እወቅ አሉት።
ትንቢተ ዳንኤል 3 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ ዳንኤል 3:8-18
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos