ትንቢተ ዳንኤል 2:31-45

ትንቢተ ዳንኤል 2:31-45 አማ54

አንተ፥ ንጉሥ ሆይ፥ ታላቅ ምስል አየህ፥ ይህም ምስል ታላቅና ብልጭልጭታው የበዛ ነበረ፥ በፊትህም ቆሞ ነበር፥ መልኩም ግሩም ነበረ። የዚህም ምስል ራስ ጥሩ ወርቅ፥ ደረቱና ክንዶቹም ብር፥ ሆዱና ወገቡም ናስ፥ ጭኖቹም ብረት፥ እግሮቹም እኩሉ ብረት እኩሉም ሸክላ ነበረ። እጅም ሳይነካው ድንጋይ ከተራራው ተፈንቅሎ ከብረትና ከሸክላ የሆነውን የምስሉን እግሮች ሲመታና ሲፈጭ አየህ። የዚያን ጊዜም ብረቱና ሸክላው፥ ናሱና ብሩ ወርቁም በአንድነት ተፈጨ፥ በመከርም ጊዜ በአውድማ ላይ እንዳለ እብቅ ሆነ፥ ነፋስም ወሰደው፥ ቦታውም አልታወቀም፥ ምስሉንም የመታ ድንጋይ ታላቅ ተራራ ሆነ ምድርንም ፈጽሞ ሞላ። ሕልሙ ይህ ነው፥ አሁንም ፍቺውን በንጉሡ ፊት እንናገራለን። አንተ፥ ንጉሥ ሆይ፥ የሰማይ አምላክ መንግሥትንና ኃይልን፥ ብርታትንና ክብርን የሰጠህ የነገሥታት ንጉሥ አንተ ነህ። በሚቀመጡበትም ስፍራ ሁሉ የሰው ልጆችንና የምድር አራዊትን የሰማይ ወፎችንም በእጅህ አሳልፎ ሰጥቶሃል፥ ለሁሉም ገዥ አድርጎሃል አንተ የወርቁ ራስ ነህ። ከአንተም በኋላ ከአንተ የሚያንስ ሌላ መንግሥት ይነሣል፥ ከዚያም በኋላ በምድር ሁሉ ላይ የሚገዛ ሌላ ሦስተኛ የናስ መንግሥት ይነሣል። አራተኛውም መንግሥት ሁሉን እንደሚቀጠቅጥና እንደሚያደቅቅ ብረት ይበረታል፥ እነዚህንም ሁሉ እንደሚፈጭ ብረት ይቀጠቅጣል ይፈጭማል። እግሮቹና ጣቶቹም እኩሉ ሸክላ እኩሉም ብረት ሆኖ እንዳየህ፥ እንዲሁ የተከፋፈለ መንግሥት ይሆናል፥ ብረቱም ከሸክላው ጋር ተደባልቆ እንዳየሁ፥ የብረት ብርታት ለእርሱ ይሆናል። የእግሮቹም ጣቶች እኩሉ ብረት እኩሉም ሸክላ እንደ ነበሩ፥ እንዲሁም መንግሥቱ እኩሉ ብርቱ እኩሉ ደካማ ይሆናል። ብረቱም ከሸክላው ጋር ተደባልቆ እንዳየህ፥ እንዲሁ ከሰው ዘር ጋር ይደባለቃሉ፥ ነገር ግን ብረት ከሸክላ ጋር እንደማይጣበቅ፥ እንዲሁ እርስ በርሳቸው አይጣበቁም። በእነዚያም ነገሥታት ዘመን የሰማይ አምላክ ለዘላለም የማይፈርስ መንግሥት ያስነሣል፥ ለሌላ ሕዝብም የማይሰጥ መንግሥት ይሆናል፥ እነዚያንም መንግሥታት ሁሉ ትፈጫቸዋለች ታጠፋቸውማለች፥ ለዘላለምም ትቆማለች። ድንጋዩም እጅ ሳይነካው ከተራራ ተፈንቅሎ ብረቱንና ናሱን ሸክላውንና ብሩን ወርቁንም ሲፈጨው እንዳየህ፥ እንዲሁ ከዚህ በኋላ የሚሆነውን ታላቁ አምላክ ለንጉሡ አስታውቆታል፥ ሕልሙም እውነተኛ ፍቺውም የታመነ ነው።