ዳንኤል 2:31-45
ዳንኤል 2:31-45 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“ንጉሥ ሆይ፤ በፊት ለፊትህ ግዙፍ የሆነ፣ የሚያብረቀርቅና የሚያስፈራ ታላቅ ምስል ቆሞ አየህ፤ የምስሉ ራስ ከንጹሕ ወርቅ፣ ደረቱና ክንዶቹ ከብር፣ ሆዱና ጭኖቹ ከናስ የተሠሩ ነበሩ፤ ቅልጥሞቹም ከብረት፣ እግሮቹም ከፊሉ ከብረት፣ ከፊሉም ከሸክላ የተሠሩ ነበሩ። ይህን በመመልከት ላይ ሳለህ፣ አንድ ድንጋይ የሰው እጅ ሳይነካው ተፈንቅሎ ወረደ፤ ከብረትና ከሸክላ የተሠሩትን የምስሉን እግሮች መታቸው፤ አደቀቃቸውም። ወዲያውኑም ብረቱ፣ ሸክላው፣ ናሱ፣ ብሩና ወርቁ ተሰባበሩ፤ በበጋ ወራት በዐውድማ ላይ እንደሚገኝ እብቅም ሆኑ፤ ነፋስም አንዳች ሳያስቀር ጠራረጋቸው፤ ምስሉን የመታው ድንጋይ ግን ታላቅ ተራራ ሆነ፤ ምድርንም ሞላ። “ሕልሙ ይህ ነበር፤ አሁን ትርጕሙን ለንጉሥ እንናገራለን። ንጉሥ ሆይ፤ አንተ የነገሥታት ንጉሥ ነህ፤ የሰማይ አምላክ መንግሥትንና ሥልጣንን፣ ኀይልንና ክብርን ሰጥቶሃል፤ የሰው ልጆችን፣ የምድር አራዊትንና የሰማይ ወፎችን በእጅህ አሳልፎ ሰጥቶሃል፤ በየትም ቦታ ቢሆኑ፣ በሁሉም ላይ ገዥ አድርጎሃል፤ እንግዲህ የወርቁ ራስ አንተ ነህ። “ከአንተም በኋላ ከአንተ የሚያንስ ሌላ መንግሥት ይነሣል፤ ቀጥሎም በናስ የተመሰለው ሦስተኛ መንግሥት ይነሣል፤ መላውን ምድርም ይገዛል። በመጨረሻም ሁሉን ነገር እንደሚቀጠቅጥና እንደሚሰብር ብረት ብርቱ የሆነ አራተኛ መንግሥት ይነሣል፤ ብረት ሁሉን ሰባብሮ እንደሚያደቅ ከርሱ በፊት የነበሩትን መንግሥታት ሁሉ ሰባብሮ ያደቅቃቸዋል። እግሮቹና ጣቶቹ ከፊል ብረትና ከፊል ሸክላ ሆነው እንዳየህ፣ እንዲሁ የተከፋፈለ መንግሥት ይሆናል፤ ነገር ግን ብረትና ሸክላ ተደባልቀው እንዳየህ በከፊል የብረት ጥንካሬ ይኖረዋል። የእግሮቹ ጣቶች ከፊሉ ብረት ከፊሉ ሸክላ እንደ ሆኑ ሁሉ ይህም መንግሥት በከፊሉ ብርቱ በከፊሉ ደካማ ይሆናል። ብረትና ሸክላ ተደባልቀው እንዳየህ ሁሉ ሕዝቡም ድብልቅ ይሆናል፤ ብረትና ሸክላ እንደማይዋሃድ ሁሉ ሕዝቡም በአንድነት አይኖሩም። “በእነዚያ ነገሥታት ዘመን፣ የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይፈርስና ለሌላም ሕዝብ የማይሰጥ መንግሥት ይመሠርታል፤ እነዚያን መንግሥታት ሁሉ ያደቅቃል፤ እስከ መጨረሻውም ያጠፋቸዋል፤ ይህ መንግሥት ራሱ ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል። የሰው እጅ ሳይነካው ከተራራ ተፈንቅሎ የወረደውና ብረቱን፣ ናሱን፣ ሸክላውን፣ ብሩንና ወርቁን ያደቀቀው ድንጋይ ራእይ ትርጓሜ ይህ ነው፤ “ታላቁ አምላክ ወደ ፊት የሚሆነውን ለንጉሡ አሳይቶታል፤ ሕልሙ እውነት ነው፤ ትርጓሜውም የታመነ ነው።”
ዳንኤል 2:31-45 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
አንተ፥ ንጉሥ ሆይ፥ ታላቅ ምስል አየህ፥ ይህም ምስል ታላቅና ብልጭልጭታው የበዛ ነበረ፥ በፊትህም ቆሞ ነበር፥ መልኩም ግሩም ነበረ። የዚህም ምስል ራስ ጥሩ ወርቅ፥ ደረቱና ክንዶቹም ብር፥ ሆዱና ወገቡም ናስ፥ ጭኖቹም ብረት፥ እግሮቹም እኩሉ ብረት እኩሉም ሸክላ ነበረ። እጅም ሳይነካው ድንጋይ ከተራራው ተፈንቅሎ ከብረትና ከሸክላ የሆነውን የምስሉን እግሮች ሲመታና ሲፈጭ አየህ። የዚያን ጊዜም ብረቱና ሸክላው፥ ናሱና ብሩ ወርቁም በአንድነት ተፈጨ፥ በመከርም ጊዜ በአውድማ ላይ እንዳለ እብቅ ሆነ፥ ነፋስም ወሰደው፥ ቦታውም አልታወቀም፥ ምስሉንም የመታ ድንጋይ ታላቅ ተራራ ሆነ ምድርንም ፈጽሞ ሞላ። ሕልሙ ይህ ነው፥ አሁንም ፍቺውን በንጉሡ ፊት እንናገራለን። አንተ፥ ንጉሥ ሆይ፥ የሰማይ አምላክ መንግሥትንና ኃይልን፥ ብርታትንና ክብርን የሰጠህ የነገሥታት ንጉሥ አንተ ነህ። በሚቀመጡበትም ስፍራ ሁሉ የሰው ልጆችንና የምድር አራዊትን የሰማይ ወፎችንም በእጅህ አሳልፎ ሰጥቶሃል፥ ለሁሉም ገዥ አድርጎሃል አንተ የወርቁ ራስ ነህ። ከአንተም በኋላ ከአንተ የሚያንስ ሌላ መንግሥት ይነሣል፥ ከዚያም በኋላ በምድር ሁሉ ላይ የሚገዛ ሌላ ሦስተኛ የናስ መንግሥት ይነሣል። አራተኛውም መንግሥት ሁሉን እንደሚቀጠቅጥና እንደሚያደቅቅ ብረት ይበረታል፥ እነዚህንም ሁሉ እንደሚፈጭ ብረት ይቀጠቅጣል ይፈጭማል። እግሮቹና ጣቶቹም እኩሉ ሸክላ እኩሉም ብረት ሆኖ እንዳየህ፥ እንዲሁ የተከፋፈለ መንግሥት ይሆናል፥ ብረቱም ከሸክላው ጋር ተደባልቆ እንዳየሁ፥ የብረት ብርታት ለእርሱ ይሆናል። የእግሮቹም ጣቶች እኩሉ ብረት እኩሉም ሸክላ እንደ ነበሩ፥ እንዲሁም መንግሥቱ እኩሉ ብርቱ እኩሉ ደካማ ይሆናል። ብረቱም ከሸክላው ጋር ተደባልቆ እንዳየህ፥ እንዲሁ ከሰው ዘር ጋር ይደባለቃሉ፥ ነገር ግን ብረት ከሸክላ ጋር እንደማይጣበቅ፥ እንዲሁ እርስ በርሳቸው አይጣበቁም። በእነዚያም ነገሥታት ዘመን የሰማይ አምላክ ለዘላለም የማይፈርስ መንግሥት ያስነሣል፥ ለሌላ ሕዝብም የማይሰጥ መንግሥት ይሆናል፥ እነዚያንም መንግሥታት ሁሉ ትፈጫቸዋለች ታጠፋቸውማለች፥ ለዘላለምም ትቆማለች። ድንጋዩም እጅ ሳይነካው ከተራራ ተፈንቅሎ ብረቱንና ናሱን ሸክላውንና ብሩን ወርቁንም ሲፈጨው እንዳየህ፥ እንዲሁ ከዚህ በኋላ የሚሆነውን ታላቁ አምላክ ለንጉሡ አስታውቆታል፥ ሕልሙም እውነተኛ ፍቺውም የታመነ ነው።
ዳንኤል 2:31-45 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
“ንጉሥ ሆይ! እጅግ የሚያንጸባርቅና ብልጭልጭታው ለማየት የሚያስፈራ ታላቅ ምስል በፊትህ ቆሞ አየህ። የምስሉ ራስ ከንጹሕ ወርቅ፥ ደረቱና እጆቹ ከብር፥ ሆዱና ጭኖቹ ከነሐስ፤ ቅልጥሞቹ ከብረት፥ እግሮቹ እኩሌታው ከብረት፥ እኩሌታው ከሸክላ የተሠሩ ነበሩ። አንተ ምስሉን ስትመለከት ሳለ ታላቅ ድንጋይ የሰው እጅ ሳይነካው ተፈንቅሎ ወረደ፤ ከብረትና ከሸክላ በተሠሩት በምስሉ እግሮች ላይ ወድቆ ሰባበራቸው። ብረቱ፥ ሸክላው፥ ነሐሱ፥ ብሩና ወርቁ ሁሉ ወዲያውኑ ተንከታክቶ በበጋ ወራት በአውድማ ላይ እንደሚገኝ እብቅ ሆነ፤ ምንም ሳያስቀር ነፋስ ጠራርጎ ወሰደው፤ በምስሉ ላይ የወደቀው ድንጋይ ግን ምድርን ሁሉ እስኪሞላ ድረስ ከፍ ከፍ ብሎ ታላቅ ተራራ ሆነ። “እነሆ፥ ሕልሙ ይህ ነው፤ ትርጒሙም እንደሚከተለው ነው፤ ንጉሥ ሆይ! አንተ ከሁሉ የምትበልጥ ንጉሠ ነገሥት ነህ፤ የሰማይ አምላክ መንግሥትንና ኀይልን፤ ሥልጣንና ክብርን ሰጥቶሃል። በምድር ሁሉ ላይ ገዢ አድርጎሃል፤ በሰው፥ በእንስሶችና በወፎች ላይ ሥልጣን ሰጥቶሃል፤ ስለዚህ የወርቁ ራስ አንተ ነህ። ከአንተ በኋላ በገናናነቱ የአንተን መንግሥት የሚያኽል አነስተኛ መንግሥት ይነሣል፤ ከእርሱም ቀጥሎ ዓለምን ሁሉ የሚገዛ በነሐስ የሚመሰል መንግሥት በሦስተኛ ደረጃ ይነሣል። እንደገናም ሁሉን ነገር የሚሰባብርና የሚያንከታክት እንደ ብረት የጠነከረ አራተኛ መንግሥት ይነሣል፤ ብረት ሁሉን ነገር ሰባብሮ እንደሚያደቅ፥ እርሱም ከእርሱ በፊት የነበሩትን መንግሥታት ሁሉ ሰባብሮ ያደቃል። እግሮቹና የእግሮቹ ጣቶች አሠራር እኩሌታው ከብረት፥ እኩሌታው ከሸክላ መሆኑን አይተሃል፤ ይህም የሚያመለክተው ያ መንግሥት የተከፋፈለ መሆኑን ነው፤ ብረት ከሸክላ ጋር ተደባልቆ እንዳየህ፥ ያ መንግሥት በከፊል እንደ ብረት የጠነከረ ይሆናል። የእግሮቹ ጣቶች አሠራር እኩሌታው ብረት፥ እኩሌታው ሸክላ እንደ ሆነ እንዲሁም ያም መንግሥት በከፊል ብርቱ፥ በከፊል ደካማ ይሆናል። ብረቱ ከሸክላ ጋር ተደባልቆ እንዳየህ የእነዚያ የሁለት መንግሥታት ሕዝቦች እርስ በርሳቸው በመጋባት ይደባለቃሉ፤ ሆኖም ብረት ከሸክላ መዋሐድ እንደማይችል እነርሱም አንድ መሆን አይችሉም፤ በእነዚያም ነገሥታት ዘመን የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይፈርስና ግዛቱም በሌላ ሕዝብ የማይደፈር መንግሥትን ይመሠርታል፤ ይህ መንግሥት ሌሎችን መንግሥታት እስከ መጨረሻው ያጠፋቸዋል፤ እርሱ ግን ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖራል፤ የሰው እጅ ሳይነካው ከተራራ ላይ ተፈንቅሎ በመውረድ ከብረት፥ ከነሐስ፥ ከሸክላ፥ ከብርና ከወርቅ የተሠራውን ምስል ያደቀቀውም ድንጋይ፥ ያ መንግሥት ነው፤ በዚህም ታላቁ አምላክ ወደፊት የሚሆነውን ሁሉ አሳይቶሃል፤ እነሆ፥ ሕልሙ እውነት ነው፤ አስተማማኝ ትርጒሙም ይኸው ነው።”