ትንቢተ ዳንኤል 2:17-23

ትንቢተ ዳንኤል 2:17-23 አማ54

የዚያን ጊዜም ዳንኤል ወደ ቤቱ ሄደ። ዳንኤልም ባልንጀሮቹም ከቀሩት ከባቢሎን ጠቢባን ጋር እንዳይሞቱ ስለዚህ ምሥጢር ምሕረትን ከሰማይ አምላክ ይለምኑ ዘንድ ነገሩን ለባልንጀሮቹ ለአናንያና ለሚሳኤል ለአዛርያ አስታወቃቸው። የዚያን ጊዜም ምሥጢሩ በሌሊት ራእይ ለዳንኤል ተገለጠለት፥ ዳንኤልም የሰማይን አምላክ አመሰገነ። ዳንኤልም ተናገረ እንዲህም አለ፦ ጥበብና ኃይል ለእርሱ ነውና የእግዚአብሔር ስም ከዘላለም እስከ ዘላለም ይባረክ፥ ጊዜያትንና ዘመናትን ይለውጣል፥ ነገሥታትን ያፈልሳል፥ ነገሥታትንም ያስነሣል፥ ጥበብን ለጠቢባን እውቀትንም ለአስተዋዮች ይሰጣል። የጠለቀውንና የተሠወረውን ይገልጣል፥ በጨለማ ያለውን ያውቃል፥ ብርሃንም ከእርሱ ጋር ነው። ጥበብንና ኃይልን የሰጠኸኝ፥ እኛም የለመንንህን ነገር አሁን ያስታወቅኸኝ፥ አንተ የአባቶቼ አምላክ ሆይ፥ የንጉሡን ነገር አስታውቀኸኛልና እገዛልሃለሁ አመሰግንህማለሁ።