ትንቢተ ዳንኤል 2:17-23

ትንቢተ ዳንኤል 2:17-23 አማ05

ከዚህ በኋላ ዳንኤል ወደ ቤቱ ሄደና የሆነውን ነገር ለጓደኞቹ ለሐናንያ፥ ለሚሳኤልና ለዐዛርያ ነገራቸው። እነርሱም ከቀሩት የባቢሎን ጠቢባን ጋር እንዳይገደሉ የሰማይ አምላክ ምሕረት እንዲያደርግላቸውና ምሥጢሩንም እንዲገልጥላቸው ይለምኑት ዘንድ አሳሰባቸው። በዚያኑ ሌሊት ምሥጢሩ ለዳንኤል በራእይ ተገለጠለት፤ ስለዚህ የሰማይን አምላክ እንዲህ ሲል አመሰገነ፦ “ጥበብም ኀይልም የእርሱ ስለ ሆነ እግዚአብሔር ለዘለዓለም የተመሰገነ ይሁን! እርሱ ጊዜያትንና ወራትን ያፈራርቃል፤ ነገሥታትን ወደ ዙፋን ያወጣል፤ ከዙፋንም ያወርዳል፤ ጥበብን ለጠቢባን፥ ዕውቀትንም ለአስተዋዮች የሚሰጥ እርሱ ነው። እርሱ ጥልቅ የሆነውን ምሥጢርና የተሰወረውን ነገር ይገልጣል፤ በእርሱ ዘንድ ሁልጊዜ ብርሃን ስላለ፥ በጨለማ የተሰወረውን ያውቃል። የቀድሞ አባቶቼ አምላክ ሆይ! አመሰግንሃለሁ፤ ከፍ ከፍም አደርግሃለሁ፤ አንተ ጥበብንና ኀይልን ሰጥተኸኛል፤ ጸሎታችንንም ሰምተህ የንጉሡን ሕልም ገልጠህልናል።”