የሐዋርያት ሥራ 7:44-60

የሐዋርያት ሥራ 7:44-60 አማ54

እንዳየው ምስል አድርጎ ይሠራት ዘንድ ሙሴን ተናግሮ እንዳዘዘው፥ የምስክር ድንኳን ከአባቶቻችን ዘንድ በምድረ በዳ ነበረች፤ አባቶቻችንም ደግሞ በተራ ተቀብለው እግዚአብሔር በፊታቸው ያወጣቸውን የአሕዛብን አገር በያዙት ጊዜ ከኢያሱ ጋር አገቡአት፥ እስከ ዳዊት ዘመንም ድረስ ኖረች። እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ አግኝቶ ለያዕቆብ አምላክ ማደሪያን ያገኝ ዘንድ ለመነ። ነገር ግን ሰሎሞን ቤት ሠራለት። ነገር ግን ነቢዩ፦ ‘ሰማይ ዙፋኔ ነው ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት፤ ለእኔ ምን ዓይነት ቤት ትሠራላችሁ?’ ይላል ጌታ፥ ወይስ የማርፍበት ስፍራ ምንድር ነው? ይህንስ ሁሉ እጄ የሠራችው አይደለምን? እንዳለ፥ ልዑል የሰው እጅ በሠራችው አይኖርም። እናንተ አንገተ ደንዳኖች ልባችሁና ጆሮአችሁም ያልተገረዘ፥ እናንተ ሁልጊዜ መንፈስ ቅዱስን ትቃወማላችሁ፤ አባቶቻችሁ እንደ ተቃወሙት እናንተ ደግሞ። ከነቢያትስ አባቶቻችሁ ያላሳደዱት ማን ነው? የጻድቁንም መምጣት አስቀድሞ የተናገሩትን ገደሉአቸው፤ በመላእክት ሥርዓት ሕግን ተቀብላችሁ ያልጠበቃችሁት እናንተም አሁን እርሱን አሳልፋችሁ ሰጣችሁት ገደላችሁትም።” ይህንም በሰሙ ጊዜ በልባቸው በጣም ተቈጡ ጥርሳቸውንም አፋጩበት። መንፈስ ቅዱስንም ተሞልቶ ወደ ሰማይ ትኵር ብሎ ሲመለከት የእግዚአብሔርን ክብር ኢየሱስንም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየና፦ “እነሆ፥ ሰማያት ተከፍተው የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ” አለ። በታላቅ ድምፅም እየጮኹ ጆሮአቸውን ደፈኑ፥ በአንድ ልብ ሆነውም ወደ እርሱ ሮጡ፥ ከከተማም ወደ ውጭ አውጥተው ወገሩት። ምስክሮችም ልብሳቸውን ሳውል በሚሉት በአንድ ጎበዝ እግር አጠገብ አኖሩ። እስጢፋኖስም፦ “ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ ነፍሴን ተቀበል” ብሎ ሲጠራ ይወግሩት ነበር። ተንበርክኮም፦ “ጌታ ሆይ፥ ይህን ኃጢአት አትቍጠርባቸው ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ይህንም ብሎ አንቀላፋ። ሳውልም በእርሱ መገደል ተስማምቶ ነበር።