“አባቶቻችን በበረሓ የምስክሩ ድንኳን ነበረቻቸው፤ ይህችንም ድንኳን እግዚአብሔር በነገረውና ባሳየው መሠረት የሠራት ሙሴ ነበር። እግዚአብሔር ከፊታቸው ያባረረላቸውን የአሕዛብን አገር በወረሱ ጊዜ አባቶቻችን ይህችን የተቀበሉአትን ድንኳን ከኢያሱ ጋር ወደዚያ አገቡአት፤ እስከ ዳዊት ዘመንም ድረስ እዚያ ኖረች። ዳዊትም በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ አግኝቶ ለያዕቆብ አምላክ ለእግዚአብሔር ማደሪያ የሚሆን ቤት ለመሥራት በጸሎት ለመነ። ነገር ግን ለእግዚአብሔር ቤት የሠራው ሰሎሞን ነው። “ሆኖም ልዑል እግዚአብሔር በሰው እጅ በተሠራ ቤት ውስጥ አይኖርም፤ ይህም ነቢዩ እንዲህ ሲል እንደ ጻፈው ነው፤ ‘ሰማይ ዙፋኔ ነው፤ ምድርም የእግሬ ማሳረፊያ ናት፤ ታዲያ ለእኔ ምን ዐይነት ቤት ትሠሩልኛላችሁ? የማርፍበትስ ቦታ ምን ዐይነት ነው? ይላል ጌታ። ይህን ሁሉ እኔ በእጄ የሠራሁት አይደለምን?’ ይላል እግዚአብሔር። “እናንተ እልኸኞች ልባችሁ የተደፈነ! ጆሮአችሁም የማይሰማ! እናንተም ልክ እንዳባቶቻችሁ ሁልጊዜ መንፈስ ቅዱስን ትቃወማላችሁ። ከነቢያት መካከል አባቶቻችሁ ያላሳደዱት ማን አለ? እነርሱ የጻድቁን መምጣት አስቀድመው የተናገሩትን ገደሉአቸው፤ እናንተም አሁን ይህን ጻድቁን አሳልፋችሁ በመስጠት ገደላችሁት። እናንተ በመላእክት አማካይነት ሕግን ተቀብላችሁ ነበር፤ ነገር ግን አልጠበቃችሁትም።” የሸንጎ አባሎች ይህን በሰሙ ጊዜ ተናደዱ፤ በእስጢፋኖስ ላይም በቊጣ ጥርሳቸውን አፋጩ። እርሱ ግን በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ወደ ሰማይ ትኲር ብሎ ሲመለከት የእግዚአብሔርን ክብር አየ፤ ኢየሱስንም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየው፤ ስለዚህ “እነሆ፥ ሰማይ ተከፍቶ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ” አለ። በዚህ ጊዜ እነርሱ በታላቅ ድምፅ ጮኹ፤ ጆሮአቸውንም ደፍነው በአንድነት ወደ እርሱ ሮጡ። ከከተማ አወጡትና በድንጋይ ወገሩት፤ ምስክሮችም ልብሳቸውን ወስደው ሳውል የሚባል አንድ ጐልማሳ እንዲጠብቅላቸው በእግሩ ሥር አስቀመጡ። በድንጋይ ሲወግሩት ሳሉ እስጢፋኖስ፥ “ጌታ ኢየሱስ ሆይ! ነፍሴን ተቀበል!” ብሎ ጸለየ። ተንበርክኮም “ጌታ ሆይ! ይህን በደል አትቊጠርባቸው!” ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ይህንንም ብሎ ሞተ።
የሐዋርያት ሥራ 7 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሐዋርያት ሥራ 7:44-60
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች