የሐዋርያት ሥራ 7:20-43

የሐዋርያት ሥራ 7:20-43 አማ54

በዚያን ጊዜ ሙሴ ተወለደ በእግዚአብሔርም ፊት ያማረ ነበር፤ በአባቱ ቤትም ሦስት ወር አደገ፤ በተጣለም ጊዜ የፈርዖን ልጅ አነሣችው ልጅም ይሆናት ዘንድ አሳደገችው። ሙሴም የግብፆችን ጥበብ ሁሉ ተማረ፥ በቃሉና በሥራውም የበረታ ሆነ። ነገር ግን አርባ ዓመት ሲሞላው ወንድሞቹን የእስራኤልን ልጆች ይጐበኝ ዘንድ በልቡ አሰበ። አንዱም ሲበደል አይቶ ረዳው፥ የግብፅን ሰውም መትቶ ለተገፋው ተበቀለ። ወንድሞቹም እግዚአብሔር በእጁ መዳንን እንዲሰጣቸው የሚያስተውሉ ይመስለው ነበር፥ እነርሱ ግን አላስተዋሉም። በማግሥቱም እርስ በርሳቸው ሲጣሉ አገኛቸው፥ ሊያስታርቃቸውም ወዶ፦ ‘ሰዎች ሆይ፥ እናንተስ ወንድማማች ናችሁ፤ ስለ ምን እርስ በርሳችሁ ትበዳደላላችሁ?’ አላቸው። ያም ባልንጀራውን የሚበድል ግን፦ ‘አንተን በእኛ ላይ ሹምና ፈራጅ እንድትሆን የሾመህ ማን ነው? ወይስ ትናንትና የግብፁን ሰው እንደ ገደልኸው ልትገድለኝ ትወዳለህን?’ ብሎ ገፋው። ሙሴም ከዚህ ነገር የተነሣ ሸሽቶ በምድያም አገር መጻተኛ ሆኖ ኖረ፤ በዚያም ሁለት ልጆች ወለደ። አርባ ዓመትም ሲሞላ የጌታ መልአክ በሲና ተራራ ምድረ በዳ በቍጥቋጦ መካከል በእሳት ነበልባል ታየው። ሙሴም አይቶ ባየው ተደነቀ፤ ሊመለከትም ሲቀርብ የጌታ ቃል፦ ‘እኔ የአባቶችህ አምላክ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ’ ብሎ ወደ እርሱ መጣ። ሙሴም ተንቀጥቅጦ ሊመለከት አልደፈረም። ጌታም፦ ‘የቆምህባት ስፍራ የተቀደሰች ምድር ናትና የእግርህን ጫማ አውልቅ። በግብፅ ያሉትን የሕዝቤን መከራ ፈጽሜ አይቼ መቃተታቸውንም ሰምቼ ላድናቸው ወረድሁ፤ አሁንም ና፥ ወደ ግብፅ እልክሃለሁ’ አለው። ሹምና ፈራጅ እንድትሆን የሾመህ ማን ነው? ብለው የካዱትን፥ ይህን ሙሴን በቍጥቋጦው በታየው በመልአኩ እጅ እግዚአብሔር ሹምና ቤዛ አድርጎ ላከው። ይህ ሰው በግብፅ ምድርና በኤርትራ ባሕር በምድረ በዳም አርባ ዓመት ድንቅና ምልክት እያደረገ አወጣቸው። ይህ ሰው ለእስራኤል ልጆች፦ ‘እግዚአብሔር ከወንድሞቻችሁ እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣላችኋል፤ እርሱን ስሙት’ ያላቸው ሙሴ ነው። ይህ ሰው በሲና ተራራ ከተናገረው ምለአክና ከአባቶቻችን ጋር በምድረ በዳ በማኅበሩ ውስጥ የነበረው ነው፤ ይሰጠንም ዘንድ ሕይወት ያላቸውን ቃላት ተቀበለ፤ ለእርሱም አባቶቻችን ሊታዘዙት አልወደዱም፤ ነገር ግን ገፉት በልባቸውም ወደ ግብፅ ተመለሱ፤ አሮንንም፦ ‘በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን፤ ይህ ከግብፅ ምድር ያወጣን ሙሴ ምን እንደ ሆነ አናውቅምና’ አሉት። በዚያም ወራት ጥጃ አድረጉ ለጣዖቱም መሥዋዕት አቀረቡ፥ በእጃቸውም ሥራ ደስ አላቸው። እግዚአብሔር ግን ዘወር አለ የሰማይንም ጭፍራ ያመልኩ ዘንድ አሳልፎ ሰጣቸው፥ በነቢያትም መጽሐፍ፦ ‘እናንተ የእስራኤል ቤት፥ አርባ ዓመት በምድረ በዳ የታረደውን ከብትና መሥዋዕትን አቀረባችሁልኝን? ትሰግዱላቸውም ዘንድ የሠራችኋቸውን ምስሎች እነርሱንም የሞሎክን ድንኳንና ሬምፉም የሚሉትን የአምላካችሁን ኮከብ አነሣችሁ፤ እኔም ከባቢሎን ወዲያ እሰዳችኋለሁ’ ተብሎ እንዲህ ተጽፎአል።