በዚያን ጊዜ ሙሴ ተወለደ፤ እርሱ በእግዚአብሔር ፊት ያማረ ሕፃን ነበር፤ ሦስት ወር በአባቱ ቤት አደገ፤ ወደ ውጪም በተጣለ ጊዜ የፈርዖን ሴት ልጅ አነሣችውና እንደ ልጅዋ አድርጋ አሳደገችው። ሙሴም የግብጻውያንን ጥበብ ሁሉ ተማረ፤ በቃሉና በሥራውም የበረታ ሆነ። “ሙሴ አርባ ዓመት በሞላው ጊዜ ወንድሞቹን የእስራኤልን ልጆች ለመጐብኘት ተነሣሣ። ከወንድሞቹም አንዱ በአንድ ግብጻዊ ሰው ሲበደልና ሲገፋ አይቶ ረዳው፤ ለተገፋውም በመበቀል ግብጻዊውን መታና ገደለው። እግዚአብሔር በእርሱ አማካይነት ነጻ እንደሚያወጣቸው ወገኖቹ የሚገነዘቡ መስሎት ነበር፤ እነርሱ ግን ይህን አልተገነዘቡም። በማግስቱም ሁለት እስራኤላውያን እርስ በርሳቸው ሲጣሉ አገኘና ሊገላግላቸው በመፈለግ ‘እናንተ ሰዎች፥ እናንተ ወንድማማች ናችሁ፤ ስለምን ትጣላላችሁ?’ አላቸው። ያ ባልንጀራውን ይደበድብ የነበረው ሰው ሙሴን ወዲያ ገፈተረና ‘አንተን በእኛ ላይ ገዢና ፈራጅ ያደረገህ ማን ነው? ትናንትና ግብጻዊውን እንደ ገደልከው እኔንም ልትገድለኝ ትፈልጋለህን?’ አለው። ሙሴ ይህን በሰማ ጊዜ ከግብጽ አገር ሸሽቶ ወደ ምድያም አገር ሄደና እዚያ በስደት ኖረ፤ በዚያ ሁለት ወንዶች ልጆችን ወለደ። “ሙሴ በዚያ አገር አርባ ዓመት ካሳለፈ በኋላ በደብረ ሲና በረሓ በሚነደው የቊጥቋጦ ነበልባል ውስጥ አንድ መልአክ ታየው። ሙሴ ይህን ባየ ጊዜ ተገረመ፤ ቀረብ ብሎም ሲመለከት እንዲህ የሚለውን የጌታ ድምፅ ሰማ፤ ‘እኔ የአባቶችህ አምላክ ነኝ፤ የአብርሃም አምላክ፤ የይስሐቅ አምላክ፥ የያዕቆብ አምላክ ነኝ፤’ ሙሴም በፍርሃት ተንቀጠቀጠ፤ ለመመልከትም አልደፈረም። ጌታም እንዲህ አለው፦ ‘የቆምክበት ስፍራ የተቀደሰ ምድር ስለ ሆነ ጫማህን አውልቅ፤ በግብጽ ያለውን የሕዝቤን ጽኑ መከራ በእርግጥ አይቼአለሁ፤ የጭንቀት ጩኸታቸውንም ሰምቻለሁ፤ ስለዚህ ላድናቸው ወርጃለሁ፤ አሁንም ና! እኔ አንተን ወደ ግብጽ እልክሃለሁ።’ “የእስራኤል ሕዝብ ሙሴን ‘በእኛ ላይ ገዢና ፈራጅ እንድትሆን ያደረገህ ማን ነው?’ በማለት ተቃውመውት ነበር፤ ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ይህንኑ ሙሴን በቊጥቋጦው ውስጥ በተገለጠለት መልአክ አማካይነት ገዢና ነጻ አውጪ አድርጎ ወደ እነርሱ ላከው። በግብጽና በቀይ ባሕር ድንቆችንና ተአምራትን በማድረግ ሕዝቡን አውጥቶ አርባ ዓመት የመራቸው ይህ ሙሴ ነበር። ‘ጌታ አምላካችሁ እኔን እንዳስነሣኝ እንዲሁ ከወንድሞቻችሁ መካከል ነቢይ ያስነሣላችኋል’ ብሎ ለእስራኤላውያን የተናገረው ይኸው ሙሴ ነበር። በበረሓ ተሰብስቦ ከነበረው ሕዝብ ጋርና ከሲና ተራራ ላይ ከተናገረው መልአክ ጋር እንዲሁም ከአባቶቻችን ጋር የነበረው እርሱ ነው። የእግዚአብሔርን የሕይወት ቃል ለእኛ ያስተላለፈልንም ይኸው ሙሴ ነው። “አባቶቻችን ግን ተቃወሙት እንጂ አልታዘዙትም፤ በልባቸውም ወደ ግብጽ ለመመለስ አሰቡ። አሮንንም ‘ይህ ከግብጽ አገር ያወጣን ሙሴ ምን እንደ ደረሰበት አናውቅምና እፊት እፊታችን እየሄዱ የሚመሩንን አማልክት ሥራልን’ አሉት። በዚያን ጊዜ በጥጃ ምስል ጣዖት ሠርተው መሥዋዕት አቀረቡ፤ በእጃቸውም ሥራ ተደሰቱ። እግዚአብሔር ግን ተለያቸው። የሰማይንም ከዋክብት እንዲያመልኩ አሳልፎ ሰጣቸው፤ ይህም በነቢያት እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው፤ ‘እናንተ የእስራኤል ሰዎች ሆይ! የታረደውን እንስሳና መሥዋዕትን አርባ ዓመት ሙሉ በበረሓ ያቀረባችሁት ለእኔ ነውን? ይዛችሁ የሄዳችሁት የሞሎክን ድንኳንና ሬፋን የሚባለውን የአምላካችሁን ኮከብ ምስል ነበር፤ እነርሱም በእጃችሁ ሠርታችሁ ትሰግዱላቸው የነበሩ አማልክት ናቸው። እኔም ከባቢሎን ወዲያ እንድትሰደዱ አደርጋለሁ።’
የሐዋርያት ሥራ 7 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሐዋርያት ሥራ 7:20-43
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች