ሐዋርያት ሥራ 7:20-43

ሐዋርያት ሥራ 7:20-43 NASV

“በዚህ ጊዜ ሙሴ ተወለደ፤ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን ያገኘ ውብ ሕፃን ነበር። በአባቱም ቤት ሦስት ወር በእንክብካቤ አደገ። ወደ ውጭ በተጣለም ጊዜ የፈርዖን ልጅ አግኝታ ወሰደችው፤ እንደ ራሷ ልጅ አድርጋም አሳደገችው። ሙሴም የግብፆችን ጥበብ ሁሉ ተማረ፤ በንግግሩና በተግባሩም ብርቱ ሆነ። “ሙሴ አርባ ዓመት በሆነው ጊዜ፣ ወንድሞቹን የእስራኤልን ልጆች ሊጐበኝ በልቡ ዐሰበ። እርሱም፣ አንድ ግብጻዊ ከወገኖቹ አንዱን በደል ሲያደርስበት አይቶ ግብጻዊውንም ገደለ፤ ለተገፋው ወገኑም ተበቀለ። ወገኖቹም እግዚአብሔር በርሱ እጅ ነጻ እንደሚያወጣቸው የሚያስተውሉ መስሎት ነበር፤ እነርሱ ግን አላስተዋሉም። በማግስቱም ደግሞ ሁለት እስራኤላውያን ሲጣሉ ደረሰ፤ ሊያስታርቃቸውም ፈልጎ፣ ‘ሰዎች፤ እናንተ እኮ ወንድማማቾች ናችሁ፤ እንዴት እርስ በርሳችሁ ትጐዳዳላችሁ?’ አላቸው። “በባልንጀራው ላይ በደል ሲያደርስ የነበረው ሰው ግን፣ ሙሴን ገፈተረውና እንዲህ አለ፤ ‘አንተን በእኛ ላይ ገዥና ዳኛ አድርጎ የሾመህ ማን ነው? ትናንት ግብጻዊውን እንደ ገደልኸው እኔንም ልትገድለኝ ትፈልጋልህን?’ ሙሴም ይህን እንደ ሰማ ሸሽቶ በምድያም አገር መጻተኛ ሆኖ ተቀመጠ፤ በዚያም ሁለት ወንዶች ልጆች ወለደ። “ከአርባ ዓመት በኋላ፣ በሲና ተራራ አካባቢ ባለው ምድረ በዳ፣ በቍጥቋጦው ውስጥ በሚንቀለቀል የእሳት ነበልባል መልአክ ተገለጠለት። ሙሴም ባየው ነገር ተደነቀ፤ ነገሩን ለማጣራት ወደዚያ ሲቀርብ የጌታ ድምፅ፤ ‘እኔ የአባቶችህ አምላክ፣ የአብርሃም፣ የይሥሐቅ፣ የያዕቆብ አምላክ ነኝ’ ሲል ሰማ። ሙሴም በፍርሀት ተዋጠ፤ ለመመልከትም አልደፈረም። “ጌታም እንዲህ አለው፤ ‘የቆምህባት ስፍራ የተቀደሰች ስለ ሆነች ጫማውን ከእግርህ አውልቅ፤ በግብጽ ያለውን የሕዝቤን መከራ በርግጥ አይቻለሁ፤ የጭንቅ ጩኸታቸውን ሰምቻለሁ፤ ላድናቸውም ወርጃለሁ። አሁንም ና፤ ወደ ግብጽ መልሼ እልክሃለሁ።’ “እንግዲህ እነዚያ፣ ‘አንተን ገዥና ዳኛ አድርጎ የሾመህ ማን ነው?’ ብለው የናቁትን ይህን ሙሴ እግዚአብሔር በቍጥቋጦው ውስጥ በታየው መልአክ አማካይነት ገዥና ታዳጊ አድርጎ ወደ እነርሱ ላከው። እርሱም መርቶ ከግብጽ አወጣቸው፤ በግብጽ፣ በቀይ ባሕርና በምድረ በዳ አርባ ዓመት ድንቅ ነገሮችንና ታምራዊ ምልክቶችን አደረገ። “የእስራኤልንም ልጆች፣ ‘እግዚአብሔር እንደ እኔ ያለ ነቢይ ከወንድሞቻችሁ መካከል ያስነሣላችኋል’ ያላቸው ይኸው ሙሴ ነበር። እርሱም በሲና ተራራ ከተናገረው መልአክና ከአባቶቻችን ጋራ በምድረ በዳ በሕዝቡ ጉባኤ መካከል ነበር፤ የሕይወትንም ቃል ወደ እኛ ለማስተላለፍ ተቀበለ። “አባቶቻችን ግን ተቃወሙት እንጂ ሊታዘዙት ስላልፈለጉ በልባቸው ወደ ግብጽ ተመለሱ። አሮንንም፣ ‘በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን፤ ከግብጽ ምድር መርቶ ያወጣን ያ ሙሴ ምን እንዳገኘው አናውቅምና!’ አሉት። በዚያ ጊዜ የጥጃ ምስል ሠርተው፣ ለጣዖቱ መሥዋዕት አቀረቡ፤ በእጃቸውም ሥራ ተደሰቱ፤ ፈነጠዙም። እግዚአብሔር ግን ከእነርሱ ዘወር አለ፤ ያመልኳቸውም ዘንድ ለሰማይ ከዋክብት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ይህም በነቢያት መጽሐፍ እንዲህ ተብሎ በተጻፈው መሠረት ተፈጸመ፤ “ ‘እናንተ የእስራኤል ቤት ሆይ፤ አርባ ዓመት በምድረ በዳ፣ መሥዋዕትንና ቍርባንን አቅርባችሁልኝ ነበርን? ይልቁንም ልታመልኳቸው የሠራችኋቸውን፣ የሞሎክን ድንኳንና የኮከብ አምላክ የሆነውን የሬምፋም ጣዖት አንሥታችሁ ተሸከማችሁ። ስለዚህ ከባቢሎን ማዶ እንድትጋዙ አደርጋለሁ።’