የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የሐዋርያት ሥራ 7:1-16

የሐዋርያት ሥራ 7:1-16 አማ54

ሊቀ ካህናቱም፦ “ይህ ነገር እንዲህ ነውን?” አለው፤ እርሱም እንዲህ አለ፦ “ወንድሞችና አባቶች ሆይ፥ ስሙ። የክብር አምላክ ለአባታችን ለአብርሃም በካራን ሳይቀመጥ ገና በሁለት ወንዝ መካከል ሳለ ታየና፦ ‘ከአገርህና ከዘመዶችህም ወጥተህ ወደማሳይህ ወደ ማንኛውም ምድር ና’ አለው። በዚያን ጊዜ ከከለዳውያን አገር ወጥቶ በካራን ተቀመጠ። ከዚያም አባቱ ከሞተ በኋላ እናንተ ዛሬ ወደምትኖሩባት ወደዚች አገር አወጣው። በዚችም የእግር ጫማ ስንኳ የሚያህል ርስት አልሰጠውም፤ ነገር ግን ልጅ ሳይኖረው ለእርሱ ከእርሱም በኋላ ለዘሩ ርስት አድርጎ ይሰጠው ዘንድ ተስፋ ሰጠው። እግዚአብሔርም ዘሩ በሌላ አገር መጻተኞች እንዲሆኑ አራት መቶ ዓመትም ባሪያዎች እንዲያደርጉአቸው እንዲያስጨንቁአቸውም እንዲህ ተናገረ፤ ደግሞም እግዚአብሔር፦ ‘እንደ ባሪያዎች በሚገዙአቸው ሕዝብ ላይ እኔ እፈርድባቸዋለሁ፥ ከዚህም በኋላ ይወጣሉ በዚህም ስፍራ ያመልኩኛል’ አለ። የመገረዝንም ኪዳን ሰጠው፤ እንዲሁም ይስሐቅን ወለደ በስምንተኛውም ቀን ገረዘው ይስሐቅም ያዕቆብን ያዕቆብም አሥራ ሁለቱን የአባቶችን አለቆች። የአባቶችም አለቆች በዮሴፍ ቀንተው ወደ ግብፅ ሸጡት፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበረ፥ ከመከራውም ሁሉ አወጣው፥ በግብፅ ንጉሥ በፈርዖንም ፊት ሞገስንና ጥበብን ሰጠው፥ በግብፅና በቤቱ ሁሉ ላይም ቢትወደድ አድርጎ ሾመው። በግብፅና በከነዓንም አገር ሁሉ ራብና ብዙ ጭንቅ መጣ፥ አባቶቻችንም ምግብን አላገኙም። ያዕቆብም በግብፅ እህል መኖሩን በሰማ ጊዜ በመጀመሪያ አባቶቻችንን ሰደዳቸው፤ በሁለተኛውም ዮሴፍ ለወንድሞቹ ታወቀ፥ የዮሴፍም ትውልድ በፈርዖን ዘንድ ተገለጠ። ዮሴፍም አባቱን ያዕቆብንና ሰባ አምስት ነፍስ የነበረውን ቤተ ዘመድ ሁሉ ልኮ አስጠራ። ያዕቆብም ወደ ግብፅ ወረደ እርሱም ሞተ አባቶቻችንም፤ ወደ ሴኬምም አፍልሰው አብርሃም ከሴኬም አባት ከኤሞር ልጆች በብር በገዛው መቃብር ቀበሩአቸው።