የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሐዋርያት ሥራ 7:1-16

ሐዋርያት ሥራ 7:1-16 NASV

ሊቀ ካህናቱም፣ “ይህ የቀረበብህ ክስ እውነት ነውን?” አለው። እስጢፋኖስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ወንድሞችና አባቶች ሆይ፤ አድምጡኝ! አባታችን አብርሃም ወደ ካራን ከመምጣቱ በፊት፣ ገና በመስጴጦምያ ሳለ፣ የክብር አምላክ ተገልጦለት፣ ‘ከአገርህና ከወገንህ ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ሂድ’ አለው። “እርሱም ከከለዳውያን ምድር ወጥቶ በካራን ተቀመጠ። ከአባቱም ሞት በኋላ፣ አሁን እናንተ ወደምትኖሩበት ወደዚህ አገር አመጣው። በዚህም ስፍራ አንዲት ጫማ ታኽል እንኳ ርስት አልሰጠውም፤ ነገር ግን በዚያ ጊዜ ምንም ልጅ ሳይኖረው፣ እርሱና ከርሱም በኋላ ዘሩ ምድሪቱን እንደሚወርሱ እግዚአብሔር ቃል ገባለት። ደግሞም እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ተናገረው፤ ‘ዘርህ በባዕድ አገር መጻተኛ ይሆናል፤ አራት መቶ ዓመትም በባርነት ተረግጦ ይገዛል። ነገር ግን በባርነት የሚገዛቸውን ሕዝብ እኔ ደግሞ እቀጣዋለሁ፤’ ደግሞም ‘ከዚያም አገር ወጥተው በዚህ ስፍራ ያመልኩኛል።’ ይላል እግዚአብሔር። ከዚያም የግዝረትን ኪዳን ሰጠው፤ አብርሃምም ይሥሐቅን ወለደ፤ በስምንተኛውም ቀን ገረዘው። ይሥሐቅም ያዕቆብን ወለደ፤ ያዕቆብም ዐሥራ ሁለቱን የነገድ አባቶች ወለደ። “የነገድ አባቶችም በዮሴፍ ቀንተው በባርነት ወደ ግብጽ ሸጡት፤ እግዚአብሔር ግን ከርሱ ጋራ ስለ ነበር፣ ከመከራው ሁሉ አወጣው፤ በግብጽም ንጉሥ በፈርዖን ፊት ሞገስና ጥበብን አጐናጸፈው፤ ፈርዖንም በግብጽና በቤተ መንግሥቱ ሁሉ ላይ ኀላፊ አድርጎ ሾመው። “በዚያ ጊዜም በግብጽና በከነዓን አገር ሁሉ ታላቅ መከራን ያስከተለ ራብ መጣ፤ አባቶቻችንም የሚበሉትን ዐጡ። ያዕቆብም እህል በግብጽ መኖሩን በሰማ ጊዜ፣ አባቶቻችንን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ግብጽ ላካቸው፤ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሄዱ ደግሞ ዮሴፍ ማንነቱን ለወንድሞቹ ገለጠ፤ ፈርዖንም ስለ ዮሴፍ ዘመዶች ተረዳ። ከዚህ በኋላ፣ ዮሴፍ ልኮ አባቱን ያዕቆብንና ሰባ ዐምስት ነፍስ የሚሆኑ ቤተ ዘመዶቹን በሙሉ አስመጣ። ያዕቆብ ወደ ግብጽ ወረደ፤ እርሱም አባቶቻችንም በዚያ ሞቱ። አስከሬናቸውም ወደ ሴኬም ተወስዶ፣ አብርሃም ከዔሞር ልጆች ላይ በጥሬ ብር በገዛው መቃብር ተቀበረ።