የካህናት አለቃው እስጢፋኖስን “ይህ የተባለው ነገር ልክ ነውን?” ሲል ጠየቀው። እስጢፋኖስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ወንድሞቼና አባቶቼ ሆይ! እስቲ ስሙኝ! አባታችን አብርሃም በካራን ለመኖር ከመሄዱ በፊት ገና በመስጴጦምያ ሳለ የክብር አምላክ ተገለጠለትና ‘ከአገርህ ወጥተህ፥ ከዘመዶችህ ተለይተህ፥ እኔ ወደማሳይህ አገር ሂድ’ አለው። በዚያን ጊዜ ከከለዳውያን አገር ወጥቶ በካራን ተቀመጠ፤ አባቱ ከሞተ በኋላም እግዚአብሔር ከካራን አውጥቶ ዛሬ እናንተ ወደምትኖሩባት አገር አመጣው። ይሁን እንጂ የእግር ማሳረፊያ እንኳ የሚያኽል ርስት አልሰጠውም፤ ነገር ግን ይህችን አገር ለእርሱና ከእርሱም በኋላ ለዘሩ ርስት አድርጎ እንደሚሰጠው ቃል ገብቶለት ነበር፤ ይህን ቃል የገባለትም አብርሃም ገና ልጅ ሳይኖረው ነበር። ዘሩም በባዕድ አገር ስደተኛ ሆኖ እንደሚኖርና በዚያም አገር አራት መቶ ዓመት ባሪያ አድርገው በጭቈና እንደሚገዙት ነግሮት ነበር። ቀጥሎም ‘ባሪያ አድርጎ በሚገዛው ሕዝብ ላይ እፈርድበታለሁ፤ ከዚያም በኋላ ነጻ ወጥተው በዚህ ስፍራ ያመልኩኛል’ ብሎ እግዚአብሔር ተናግሮአል። የመገረዝንም ኪዳን ሰጠው፤ ስለዚህ አብርሃም ይስሐቅን በወለደ ጊዜ በስምንተኛው ቀን ገረዘው፤ እንዲሁም ይስሐቅ ልጁን ያዕቆብን ገረዘው። ያዕቆብም የነገድ አባቶች የሆኑትን ዐሥራ ሁለቱን ልጆቹን ገረዘ። “የያዕቆብ ልጆች በወንድማቸው በዮሴፍ ላይ ቀንተው በግብጽ አገር ባሪያ እንዲሆን ሸጡት፤ እግዚአብሔር ግን ከእርሱ ጋር ነበረ፤ ከመከራው ሁሉ አወጣው፤ በግብጽ ንጉሥ በፈርዖን ፊትም ሞገስንና ጥበብን ሰጠው። ንጉሡም በግብጽና በቤቱም ሁሉ ላይ አዛዥ አደረገው። በዚያን ጊዜ በግብጽና በከነዓን አገር ሁሉ ላይ ታላቅ ችግር ያስከተለ ራብ ሆነ፤ አባቶቻችንም ምግብ ሊያገኙ አልቻሉም። ያዕቆብም በግብጽ እህል መኖሩን በሰማ ጊዜ ለመጀመሪያ ጊዜ አባቶቻችንን ወደዚያ ላከ። ዳግመኛ ወደ ግብጽ ተመልሰው በሄዱ ጊዜ ዮሴፍ ለወንድሞቹ ተገለጠ፤ ቤተ ዘመዱም በፈርዖን ዘንድ ታወቀ። ከዚህ በኋላ ዮሴፍ አባቱን ያዕቆብንና ዘመዶቹን ሁሉ ወደ እርሱ አስመጣቸው፤ እነርሱም በጠቅላላው ሰባ አምስት ሰዎች ነበሩ። ስለዚህ ያዕቆብ ወደ ግብጽ ሄደ፤ እርሱና አባቶቻችን እዚያ ሞቱ። ዐጽማቸው ወደ ሴኬም ተወስዶ አብርሃም በሴኬም ከኤሞር ልጆች በገንዘቡ በገዛው መቃብር ተቀበረ።
የሐዋርያት ሥራ 7 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሐዋርያት ሥራ 7:1-16
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች