የሐዋርያት ሥራ 4:1-31

የሐዋርያት ሥራ 4:1-31 አማ54

ለሕዝቡም ሲናገሩ የካህናት አለቆችና የመቅደስ አዛዥ ሰዱቃውያንም፥ ሕዝቡን ስለ አስተማሩና በኢየሱስ የሙታንን ትንሣኤ ስለ ሰበኩ ተቸግረው፥ ወደ እነርሱ ቀረቡ፥ እጃቸውንም ጭነውባቸው አሁን መሽቶ ነበርና እስከ ማግሥቱ ድረስ በወኅኒ አኖሩአቸው። ነገር ግን ቃሉን ከሰሙት ብዙዎች አመኑ፥ የወንዶችም ቍጥር አምስት ሺህ ያህል ሆነ። በነገውም አለቆቻቸውና ሽማግሌዎች ጻፎችም ሊቀ ካህናቱ ሐናም ቀያፋም ዮሐንስም እስክንድሮስም የሊቀ ካህናቱም ዘመዶች የነበሩት ሁሉ በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ፤ እነርሱንም በመካከል አቁመው፦ “በምን ኃይል ወይስ በማን ስም እናንተ ይህን አደረጋችሁ?” ብለው ጠየቁአቸው። በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ መንፈስ ቅዱስንም ተሞልቶ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ የሕዝብ አለቆችና ሽማግሌዎች፥ እኛ ዛሬ ለድውዩ ሰው ስለ ተደረገው መልካም ሥራ ይህ በምን እንደዳነ ብንመረመር፥ እናንተ በሰቀላችሁት እግዚአብሔርም ከሙታን ባስነሣው በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ይህ ደኅና ሆኖ በፊታችሁ እንደ ቆመ፥ ለእናንተ ለሁላችሁ ለእስራኤልም ሕዝብ ሁሉ የታወቀ ይሁን። እናንተ ግንበኞች የናቃችሁት፥ የማዕዘን ራስ የሆነው ይህ ድንጋይ ነው። መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና።” ጴጥሮስና ዮሐንስም በግልጥ እንደ ተናገሩ ባዩ ጊዜ፥ መጽሐፍን የማያውቁና ያልተማሩ ሰዎች እንደ ሆኑ አስተውለው አደነቁ፥ ከኢየሱስም ጋር እንደ ነበሩ አወቁአቸው፤ የተፈወሰውንም ሰው ከእነርሱ ጋር ቆሞ ሲያዩ የሚመልሱትን አጡ። ከሸንጎም ወደ ውጭ ይወጡ ዘንድ አዝዘው፦ “በእነዚህ ሰዎች ምን እንሥራ? የታወቀ ምልክት በእነርሱ እጅ እንደ ተደረገ በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ ሁሉ ተገልጦአልና፥ እንሸሽገው ዘንድ አንችልም፤ ነገር ግን በሕዝቡ ዘንድ አብዝቶ እንዳይስፋፋ፥ ከእንግዲህ ወዲህ ለማንም ሰው በዚህ ስም እንዳይናገሩ እየዛትን እንዘዛቸው” ብለው እርስ በርሳቸው ተማከሩ። ጠርተውም በኢየሱስ ስም ፈጽመው እንዳይናገሩና እንዳያስተምሩ አዘዙአቸው። ጴጥሮስና ዮሐንስ ግን መልሰው፦ “እግዚአብሔርን ከመስማት ይልቅ እናንተን እንሰማ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት የሚገባ እንደ ሆነ ቍረጡ፤ እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ዝም ማለት አንችልም” አሉአቸው። እነርሱም እንደ ምን እንደሚቀጡ ምክንያት ስላላገኙባቸው፥ እንደ ገና ዝተው ከሕዝቡ የተነሣ ፈቱአቸው፤ ሰዎች ሁሉ ስለ ሆነው ነገር እግዚአብሔርን ያከብሩ ነበርና። ይህ የመፈወስ ምልክት የተደረገለት ሰው ከአርባ ዓመት ይበልጠው ነበርና። ተፈትተውም ወደ ወገኖቻቸው መጡና የካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች ያሉአቸውን ሁሉ ነገሩአቸው። እነርሱም በሰሙ ጊዜ በአንድ ልብ ሆነው ውፍደ እፍዚአብሔር ድምፃቸውን ከፍ አደረጉ እንዲህም አሉ፦ ጌታ ሆይ፥ አንተ ሰማዩንና ምድሩን ባሕሩንም በእነርሱም የሚኖረውን ሁሉ የፈጠርህ፥ በመንፈስ ቅዱስም በብላቴናህ በአባታችን በዳዊት አፍ፦ አሕዛብ ለምን አጕረመረሙ? ሕዝቡስ ከንቱን ነገር ለምን አሰቡ? የምድር ነገሥታት ተነሡ አለቆችም በጌታና በተቀባው ላይ አብረው ተከማቹ ብለህ የተናገር አምላክ ነህ። በቀባኸው በቅዱሱ ብላቴናህ በኢየሱስ ላይ ሄሮድስና ጴንጤናዊው ጲላጦስ ከአሕዛብና ከእስራኤል ሕዝብ ጋር፥ እጅህና አሳብህ እንዲሆን አስቀድመው የወሰኑትን ሁሉ ሊፈጽሙ፥ በዚች ከተማ በእውነት ተሰበሰቡ። አሁንም፥ ጌታ ሆይ፥ ወደ ዛቻቸው ተመልከት፤ ለመፈወስም እጅህን ስትዘረጋ በቅዱስ ብላቴናህም በኢየሱስ ስም ምልክትና ድንቅ ሲደረግ፥ ባሪያዎችህ በፍጹም ግልጥነት ቃልህን እንዲናገሩ ስጣቸው።” ከጸለዩም በኋላ ተሰብስበው የነበሩበት ስፍራ ተናወጠ፥ በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፥ የእግዚአብሔርንም ቃል በግልጥ ተናገሩ።