የሐዋርያት ሥራ 4:1-31

የሐዋርያት ሥራ 4:1-31 አማ05

ጴጥሮስና ዮሐንስ ለሕዝቡ ሲናገሩ ሳሉ ካህናትና የቤተ መቅደሱ የዘበኞች አለቃ እንዲሁም ሰዱቃውያን ወደ እነርሱ መጡና ሁለቱ ሐዋርያት የኢየሱስን ከሞት መነሣት ለሕዝቡ በማስተማራቸውና በዚህም የሙታን ትንሣኤ መኖሩን በማስረዳታቸው ተቈጡ። ስለዚህ ያዙአቸውና ጊዜው መሽቶ ስለ ነበረ እስከ ማግስቱ ድረስ በወህኒ ቤት እንዲቈዩ አደረጉአቸው። ነገር ግን ቃላቸውን ከሰሙት ሰዎች ብዙዎቹ አመኑ፤ የአመኑትም ሰዎች ቊጥር ወደ አምስት ሺህ ከፍ አለ። በማግስቱ የአይሁድ አለቆችና ሽማግሌዎች፥ የሕግ መምህራንም በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ። ከተሰበሰቡት ሰዎች መካከል የካህናት አለቃው ሐናና ቀያፋ፥ ዮሐንስና እስክንድሮስ፥ የካህናት አለቃው ቤተሰቦች ሁሉ ይገኙባቸዋል፤ እነርሱም ሁለቱን ሐዋርያት በመካከላቸው አቁመው፥ “ይህን ያደረጋችኹት በምን ኀይል ወይም በማን ስም ነው?” ሲሉ ጠየቁአቸው። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እናንተ የሕዝብ አለቆችና ሽማግሌዎች ሆይ! እኛ ዛሬ የምንጠየቀው ለአንድ ሽባ ሰው ስለ ተደረገለት መልካም ሥራና በምን ዐይነት ሁኔታ እንደ ዳነ ነው። ይህ ሰው ድኖ በፊታችሁ የቆመው እናንተ በሰቀላችሁትና እግዚአብሔር ግን ከሞት ባስነሣው በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንደ ሆነ ለእናንተ ለሁላችሁና ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ የታወቀ ይሁን። እናንተ ግንበኞች ንቃችሁ የጣላችሁትም ድንጋይ እርሱ ነው፤ ነገር ግን እርሱ የማእዘን ራስ ሆነ። ስለዚህ መዳን ከእርሱ በቀር በሌላ በማንም የለም፤ እኛ ልንድንበት የሚገባን እግዚአብሔር ለሰዎች የሰጠው ስም ከእርሱ በቀር በመላው ዓለም ማንም የለም።” ጴጥሮስና ዮሐንስ በድፍረት መናገራቸውን የሸንጎ አባሎች ባዩ ጊዜ ያልተማሩ ተራ ሰዎች መሆናቸውን ያውቁ ስለ ነበረ ተደነቁ፤ ከኢየሱስ ጋር እንደ ነበሩም ዐወቁ፤ የዳነውንም ሰው ከእነርሱ ጋር ቆሞ በማየታቸው በእነርሱ ላይ የሚሉትን አጡ። ስለዚህ ከሸንጎው ወዲያ ገለል አደረጉአቸውና በቈይታ እንዲህ ሲሉ ተማከሩ። “እንግዲህ በእነዚህ ሰዎች ላይ ምን እናድርግ? ይህ ታላቅ ተአምር በእነርሱ እጅ መደረጉ በኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ሁሉ ታውቆአል፤ ስለዚህ ልንክደው አንችልም። ነገር ግን በሕዝቡ ዘንድ እየተስፋፋ እንዳይሄድ ከእንግዲህ ወዲህ የኢየሱስን ስም በመጥራት ለማንም እንዳይናገሩ፥ እናስጠንቅቃቸው።” ከዚህ በኋላ ጠሩአቸውና የኢየሱስን ስም በመጥራት ከቶ እንዳይናገሩ ወይም እንዳያስተምሩ በጥብቅ አዘዙአቸው። ጴጥሮስና ዮሐንስ ግን እንዲህ ሲሉ መለሱላቸው፦ “ለእግዚአብሔር ከመታዘዝ ይልቅ ለእናንተ መታዘዝ በእግዚአብሔር ፊት ተገቢ ነውን? እስቲ እናንተ ራሳችሁ ፍረዱ። እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር አንቈጠብም።” የሕዝብ አለቆችና የሸንጎው አባሎች ጴጥሮስንና ዮሐንስን የሚያስቀጣ ምንም ምክንያት ባለማግኘታቸው፥ ሕዝቡንም ስለ ፈሩ እንደገና አስጠንቅቀው ለቀቁአቸው፤ ይህንንም ያደረጉት ሕዝቡ በሆነው ነገር እግዚአብሔርን ያመሰግን ስለ ነበር ነው። በዚህ ተአምር የተፈወሰው ያ ሰው ዕድሜው ከአርባ ዓመት በላይ ነበር። ጴጥሮስና ዮሐንስ ተለቀው ወደ ጓደኞቻቸው በተመለሱ ጊዜ የካህናት አለቆችና የአይሁድ ሽማግሌዎች ያሉአቸውን ሁሉ ነገሩአቸው። እነርሱም ይህን በሰሙ ጊዜ ድምፃቸውን በአንድነት ከፍ አድርገው ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ሲሉ ጸለዩ፤ “ሰማይን፥ ምድርን፥ ባሕርን፥ በውስጣቸው የሚኖረውን ሁሉ የፈጠርክ ልዑል እግዚአብሔር ሆይ! በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት በአገልጋይህ በአባታችን በዳዊት አፍ እንዲህ ብለህ የተናገርክ አንተ ነህ፤ ‘አሕዛብ ስለምን ተቈጡ? ሕዝቦችስ ስለምን በከንቱ ዶለቱ? የምድር ነገሥታት ተሰልፈው፥ ገዢዎችም በአንድነት ተሰብስበው፥ በጌታና በመሲሑ ላይ ተነሡ።’ “በእርግጥም ሄሮድስና ጴንጤናዊ ጲላጦስ ከአሕዛብና ከእስራኤል ሕዝብ ጋር በዚህች ከተማ ተሰብስበው መሲሕ ባደረግኸው በቅዱሱ አገልጋይህ በኢየሱስ ላይ ተነሡ፤ እንዲህም የሆነው አንተ አስቀድመህ በገዛ ኀይልህና በገዛ ፈቃድህ ያቀድከውን ለመፈጸም ነው፤ አሁንም ጌታ ሆይ፥ ዛቻቸውን ተመልከት፤ አገልጋዮችህ ቃልህን ያለ ፍርሀት በድፍረት እንዲናገሩ አድርግ፤ በቅዱሱ ልጅህ በኢየሱስ ስም በሽተኞች እንዲድኑና ተአምራትም፥ ድንቅ ነገሮችም እንዲደረጉ እጅህን ዘርጋ።” ጸሎት ከጨረሱ በኋላ ተሰብስበው የነበሩበት ስፍራ ተናወጠ፤ ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ፤ የእግዚአብሔርንም ቃል ያለ ፍርሀት በድፍረት ተናገሩ።