የሐዋርያት ሥራ 27:26-44

የሐዋርያት ሥራ 27:26-44 አማ54

ነገር ግን ወደ አንዲት ደሴት እንድንወድቅ ያስፈልገናል።” በአሥራ አራተኛውም ሌሊት በአድርያ ባሕር ወዲህና ወዲያ ስንነዳ፥ መርከበኞች በእኩለ ሌሊት ወደ አንድ ምድር የቀረቡ መሰላቸው። መለኪያ ገመድም ቢጥሉ ሀያ በሰው ቁመት አገኙ ጥቂትም ቆይተው ሁለተኛ ቢጥሉ አሥራ አምስት በሰው ቁመት አገኙ፤ ድንጋያማም ወደ ሆነ ስፍራ እንዳይወድቁ ፈርተው፥ ከመርከቡ በስተኋላ አራት መልሕቅ አወረዱ፥ ቀንም እንዲሆን ተመኙ። መርከበኞቹም ከመርከቡ ይሸሹ ዘንድ ፈልገው ከመርከቡ በስተ ፊት መልሕቅ መጣል እንዳላቸው አመካኝተው ታንኳይቱን ወደ ባሕር ባወረዱ ጊዜ፥ ጳውሎስ ለመቶ አለቃውና ለወታደሮቹ፦ “እነዚህ በመርከቡ ካልቆዩ እናንተ ትድኑ ዘንድ አትችሉም” አላቸው። ያን ጊዜ ወታደሮቹ የታንኳይቱን ገመድ ቈርጠው ትወድቅ ዘንድ ተዉአት። ቀንም ሲነጋ ጳውሎስ ምግብ ይበሉ ዘንድ ሁሉን ይለምን ነበር፥ እንዲህም አላቸው፦ “እየጠበቃችሁ ምንም ሳትቀበሉ ጦማችሁን ከሰነበታችሁ ዛሬ አሥራ አራተኛ ቀናችሁ ነው። ሰለዚህ ምግብ ትበሉ ዘንድ እለምናችኋለሁ፤ ይህ ለደኅንነታችሁ ይሆናልና፤ ከእናንተ ከአንዱ የራስ ጠጕር እንኳ አትጠፋምና።” ይህንም ብሎ እንጀራን ይዞ በሁሉ ፊት እግዚአብሔርን አመሰገነ ቈርሶም ይበላ ዘንድ ጀመረ። ሁለም ተጽናንተው ራሳቸው ደግሞ ምግብ ተቀበሉ። በመርከቡም ያለን ሁላችን ሁለት መቶ ሰባ ስድስት ነፍስ ነበርን። በልተውም በጠገቡ ጊዜ ስንዴውን ወደ ባሕር እየጣሉ መርከቡን አቃለሉት። በነጋም ጊዜ ምድሩን አላወቁትም፥ ነገር ግን የአሸዋ ዳር ያለውን የባሕር ስርጥ ተመለከቱ፥ ቢቻላቸውም መርከቡን ወደዚያ ይገፉ ዘንድ ቈረጡ። መልሕቆቹንም ፈትተው በባሕር ተዉአቸው፥ ያን ጊዜም የመቅዘፊያውን ማሠሪያ ፈቱት፤ ታናሹንም ሸራ ለነፋስ ከፍ አድርገው ወደ ዳር አቅንተው ይሄዱ ዘንድ ጀመሩ። ነገር ግን ሁለት ባሕር በተገናኙበት ስፍራ ወድቀው መርከቡን በዲብ ላይ ነዱ፤ በስተ ፊቱም ተተክሎ የማይነቃነቅ ሆነ፥ በስተ ኋላው ግን ከማዕበሉ ግፊያ የተነሣ ይሰበር ነበር። ወታደሮቹም ከእስረኞች አንድ ስንኳ ዋኝቶ እንዳያመልጥ ይገድሉአቸው ዘንድ ተማከሩ። የመቶ አለቃው ግን ጳውሎስን ያድነው ዘንድ አስቦ ምክራቸውን ከለከለ፤ ዋና የሚያውቁትም ከመርከብ ራሳቸውን እየወረወሩ አስቀድመው ወደ ምድር ይወጡ ዘንድ፥ የቀሩትም እኵሌቶቹ በሳንቃዎች ላይ እኵሌቶቹም በመርከቡ ስባሪ ይወጡ ዘንድ አዘዘ። እንዲሁም ሁሉ በደኅና ወደ ምድር ደረሱ።