ሆኖም ነፋሱ ወደ አንዲት ደሴት ዳርቻ ወስዶ ይጥለናል።” በዐሥራ አራተኛው ሌሊት በአድርያ ባሕር መካከል ላይ በነፋስ እየተንገላታን ስንሄድ እኩለ ሌሊት ላይ መርከበኞች ወደ ምድር የቀረቡ መሰላቸው። ስለዚህ የባሕር ጥልቀት መለኪያ ገመድ ሲጥሉ የባሕሩ ጥልቀት አርባ ሜትር ያኽል ሆኖ ተገኘ፤ ጥቂት ቈይተው መለኪያውን እንደገና በጣሉ ጊዜ ሠላሳ ሜትር ያኽል ጥልቀት አገኙ። መርከባችን በባሕሩ ዳር ካሉ ድንጋዮች እንዳይጋጭ ፈርተው ከመርከቡ በስተኋላ አራት መልሕቆችን ወደ ባሕሩ አወረዱ፤ ከዚህ በኋላ ሌሊቱ አልፎ ቀን እንዲመጣላቸው ይጸልዩ ጀመር። መርከበኞቹ ከመርከቡ ወጥተው ለመሸሽ ፈልገው ስለ ነበር በመርከቡ በስተፊት መልሕቆችን የሚጥሉ መስለው በመርከቡ ላይ የነበረችውን ጀልባ ወደ ባሕሩ ጣሉ። በዚህ ጊዜ ጳውሎስ መቶ አለቃውንና ወታደሮቹን “እነዚህ መርከበኞች በመርከቡ ላይ ዐርፈው ካልተቀመጡ እናንተ ለመዳን አትችሉም” አላቸው። ስለዚህ ወታደሮቹ ጀልባውን የያዘውን ገመድ ቈረጡና እንድትንሳፈፍ ተዉአት። ቀኑ ሊነጋ ሲል ሁሉም ምግብ እንዲመገቡ ጳውሎስ ለመናቸው፤ እንዲህም አላቸው፦ “ምንም እህል ሳትቀምሱ በመጠባበቅ ከሰነበታችሁ ዛሬ ዐሥራ አራተኛ ቀናችሁ ነው። ስለዚህ እህል እንድትቀምሱ እለምናችኋለሁ። ይህም ብርታት ይሰጣችኋል፤ ከቶ ምንም ዐይነት ጒዳት አይደርስባችሁም።” ይህንንም ካለ በኋላ እንጀራ አንሥቶ በሁሉ ፊት እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ ቈርሶም መብላት ጀመረ። በዚህ ጊዜ ሁሉም ተጽናኑና ምግብ በሉ። በመርከቡ ውስጥ በጠቅላላው ሁለት መቶ ሰባ ስድስት ሰዎች ነበርን። ሁሉም በልተው ከጠገቡ በኋላ የተጫነውን ስንዴ ወደ ባሕር በመጣል የመርከቡን ክብደት አቃለሉ። በነጋም ጊዜ የደረሱበትን ቦታ አላወቁትም፤ ነገር ግን የአሸዋ ዳርቻ ያለውን የባሕር ሰርጥ አዩ፤ የሚቻል ቢሆን መርከቡን ወደዚያ በመግፋት ወደ ዳር ለማውጣት አሰቡ። መልሕቆቹን ፈተው በባሕር ውስጥ ለቀቁአቸው፤ በዚያኑ ጊዜም የመቅዘፊያውን ገመዶች ፈቱ፤ ከዚህ በኩል ያለውን ሸራ ወደ ነፋሱ ከፍ አድርገው ወደ ባሕሩ ዳርቻ ለመውጣት ሄዱ። ነገር ግን መርከቡ ከአሸዋ ቊልል ጋር በመጋጨቱ ቊልቊል ተደፋ፤ በስተፊቱም ወደ ታች ተተክሎ የማይነቃነቅ ሆነ፤ በስተኋላው ግን ከማዕበሉ ግፊት የተነሣ ይሰባበር ጀመር። ከእስረኞቹ አንድ እንኳ ዋኝቶ እንዳያመልጥ ወታደሮቹ ሊገድሉአቸው አሰቡ። የመቶ አለቃው ግን ጳውሎስን ለማዳን ስለ ፈለገ አሳባቸውን አልተቀበለም፤ ይልቁንም መዋኘት የሚችሉ አስቀድመው ከመርከቡ ወደ ባሕር እየዘለሉ ወደ ምድር እንዲወጡ አዘዘ። የቀሩት ደግሞ በሳንቃዎችና በመርከቡ ስብርባሪዎች ላይ ሆነው እንዲወጡ አዘዘ፤ በዚህ ሁኔታ ሁሉም በደኅና ወደ ምድር ደረሱ።
የሐዋርያት ሥራ 27 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሐዋርያት ሥራ 27:26-44
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች