የሐዋርያት ሥራ 27:1-25

የሐዋርያት ሥራ 27:1-25 አማ54

ወደ ኢጣሊያም በመርከብ እንሄድ ዘንድ በተቈረጠ ጊዜ፥ ጳውሎስንና ሌሎችን እስረኞች ከአውግስጦስ ጭፍራ ለነበረ ዩልዮስ ለሚሉት ለመቶ አለቃ አሳልፈው ሰጡአቸው። በእስያም ዳርቻ ወዳሉ ስፍራዎች ይሄድ ዘንድ ባለው በአድራሚጢስ መርከብ ገብተን ተነሣን፤ የመቄዶንያም ሰው የሆነ የተሰሎንቄው አርስጥሮኮስ ከእኛ ጋር ነበረ። በነገውም ወደ ሲዶና ስንደርስ ዩልዮስ ለጳውሎስ ቸርነት አድርጎ እርዳታቸውን ይቀበል ዘንድ ወደ ወዳጆቹ እንዲሄድ ፈቀደለት። ከዚያም ተነሥተን ነፋሱ ፊት ለፊት ነበረና በቆጵሮስ ተተግነን ሄድን፤ በኪልቅያና በጵንፍልያም አጠገብ ያለውን ባሕር ከተሻገርን በኋላ በሉቅያ ወዳለ ወደ ሙራ ደረስን። የመቶ አለቃውም በዚያ ወደ ኢጣሊያ የሚሄድ የእስክንድርያውን መርከብ አግኝቶ ወደ እርሱ አገባን። ብዙ ቀንም እያዘገምን ሄደን በጭንቅ ወደ ቀኒዶስ አንጻር ደረስን፤ ነፋስም ስለ ከለከለን በቀርጤስ ተተግነን በሰልሙና አንጻር ሄድን፤ በጭንቅም ጥግ ጥጉን አልፈን ለላሲያ ከተማ ወደ ቀረበች መልካም ወደብ ወደሚሉአት ስፍራ መጣን። ብዙ ጊዜም ካለፈ በኋላ፥ የጦም ወራት አሁን አልፎ ስለ ነበረ በመርከብ ለመሄድ አሁን የሚያስፈራ ነበርና ጳውሎስ፦ “እናንተ ሰዎች ሆይ፥ ይህ ጕዞ በጥፋትና በብዙ ጕዳት እንዲሆን አያለሁ፤ ጥፋቱም በገዛ ሕይወታችን ነው እንጂ በጭነቱና በመርከቡ ብቻ አይደለም” ብሎ መከራቸው። የመቶ አለቃው ግን ጳውሎስ ከተናገረው ይልቅ የመርከብ መሪውንና የመርከቡን ባለቤት ያምን ነበር። ያም ወደብ ይከርሙበት ዘንድ የማይመች ስለ ሆነ፥ የሚበዙቱ ቢቻላቸው በሰሜንና በደቡብ ምዕራብ ትይዩ ወዳለው ፍንቄ ወደሚሉት ወደ ቀርጤስ ወደብ ደርሰው ይከርሙ ዘንድ ከዚያ እንዲነሡ መከሩ። ልከኛም የደቡብ ነፋስ በነፈሰ ጊዜ፥ እንዳሰቡት የሆነላቸው መስሎአቸው ተነሡ በቀርጤስም አጠገብ ጥግ ጥጉን አለፉ። ነገር ግን እጅግ ሳይዘገይ አውራቂስ የሚሉት ዓውሎ ነፋስ ከዚያ ወረደባቸው፤ መርከቡም ተነጥቆ ነፋሱን ሲቃወም መሄድ ስላልቻለ ለቀነው ተነዳን። ቄዳ በሚሉአትም ደሴት በተተገንን ጊዜ ታንኳይቱን ለመግዛት በጭንቅ ቻልን፤ ወደ ላይም ካወጡአት በኋላ መርከቡን በገመድ አስታጥቀው አጸኑ፤ ስርቲስም ወደሚሉት ወደ አሸዋ እንዳይወድቁ ፈርተው ሸራውን አውርደው እንዲሁ ተነዱ። ነፋሱም በርትቶ ሲያስጨንቀን በማንግሥቱ ከጭነቱ ወደ ባሕር ይጥሉ ነበር፥ በሦስተኛውም ቀን የመርከቡን ዕቃ በእጃችን ወረወርን። ብዙ ቀንም ፀሐይን ከዋክብትንም ሳናይ ትልቅ ነፋስም ሲበረታብን ጊዜ፥ ወደ ፊት እንድናለን የማለት ተስፋ ሁሉ ተቈረጠ። ሳይበሉም ብዙ ቀን ከቆዩ በኋላ፥ ያን ጊዜ ጳውሎስ በመካከላቸው ቆሞ እንዲህ አለ፦ “እናንተ ሰዎች ሆይ፥ ሰምታችሁኝ በሆነ ኖሮ ከቀርጤስ እንዳትነሡ ይህንም ጥፋትና ጕዳት እንዳታገኙ ይገባችሁ ነበር። አሁንም፦ አይዞአችሁ ብዬ እመክራችኋለሁ፤ ይህ መርከብ እንጂ ከእናንተ አንድ ነፍስ እንኳ አይጠፋምና። የእርሱ የምሆንና ደግሞ የማመልከው የእግዚአብሔር መልአክ በዚች ሌሊት በአጠገቤ ቆሞ ነበርና፥ እርሱም፦ “ጳውሎስ ሆይ፥ አትፍራ፤ በቄሣር ፊት ልትቆም ይገባሃል፤ እነሆም፥ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር የሚሄዱትን ሁሉ ሰጥቶሃል” አለኝ። ስለዚህ እናንተ ሰዎች ሆይ፥ አይዞአችሁ፤ እንደ ተናገረኝ እንዲሁ እንዲሆን እግዚአብሔርን አምናለሁ።