ወደ ኢጣሊያ እንድንሄድ በተወሰነ ጊዜ፣ ጳውሎስንና ሌሎቹን እስረኞች የንጉሠ ነገሥቱ ክፍለ ጦር አባል ለሆነው፣ ዩልዮስ ለተባለ የመቶ አለቃ አስረከቧቸው። ከአድራሚጢስ ተነሥቶ በእስያ አውራጃ ባሕር ዳርቻ ላይ ወዳሉት ወደቦች በሚሄደው መርከብ ተሳፍረን የባሕር ጕዞ ጀመርን፤ በተሰሎንቄ ይኖር የነበረው የመቄዶንያ ሰው፣ አርስጥሮኮስም ከእኛ ጋራ ነበረ። በሚቀጥለው ቀን ሲዶና ደረስን፤ ዩልዮስም ለጳውሎስ ደግነት በማሳየት ወደ ወዳጆቹ ሄዶ ርዳታ እንዲቀበል ፈቀደለት። ከዚያም ተነሥተን በባሕር ተጓዝን፤ ነፋስ ከፊት ለፊት ስለ ገጠመን፣ የቆጵሮስን ደሴት ተገን አድርገን ዐለፍን። በኪልቅያና በጵንፍልያ ዳርቻ ያለውን ባሕር ከተሻገርን በኋላ በሉቅያ አገር ሙራ የተባለ ቦታ ደረስን። ከዚያም የመቶ አለቃው ወደ ኢጣሊያ የሚሄድ የእስክንድርያ መርከብ አግኝቶ አሳፈረን። ብዙ ቀን በዝግታ እየተጓዝን ቀኒዶስ አካባቢ በጭንቅ ደረስን፤ ነፋሱም ወደ ፊት እንዳንሄድ በከለከለን ጊዜ፣ በሰልሙና አጠገብ አድርገን በቀርጤስ ተተግነን ሄድን፤ ጥግ ጥጉንም ይዘን፣ በላሲያ ከተማ አጠገብ ወዳለው፣ “መልካም ወደብ” ወደ ተባለ ስፍራ በጭንቅ ደረስን። ብዙ ጊዜ ባክኖ፤ የጾሙ ጊዜ ስላለፈ በመርከብ መጓዙ አደገኛ ሆኖ ነበርና ጳውሎስ፣ “እናንተ ሰዎች፤ ጕዞው አደገኛ እንደሚሆን፣ በመርከቡና በጭነቱ እንዲሁም በእኛ በራሳችን ላይ እንኳ ትልቅ ጕዳት እንደሚደርስ ይታየኛል” ብሎ አስጠነቀቃቸው። የመቶ አለቃው ግን ከጳውሎስ ምክር ይልቅ የመርከቡ መሪና የመርከቡ ባለቤት ያሉትን ይሰማ ነበር። ክረምቱንም በዚያ ለማሳለፍ ወደቡ አመቺ ስላልነበረ፣ አብዛኛዎቹ ፍንቄ ወደተባለው ወደብ ደርሰው በዚያ ለመክረም ተስፋ በማድረግ ጕዟችንን እንድንቀጥል ውሳኔ አስተላለፉ፤ ወደቡም በቀርጤስ ደቡብ ምዕራብና ሰሜን ምዕራብ ትይዩ የሚገኝ ነበር። መጠነኛ የደቡብ ነፋስ በነፈሰ ጊዜም እንዳሰቡት የሆነላቸው መስሏቸው መልሕቁን ነቅለው፣ የቀርጤስን ዳርቻ በመያዝ ተጓዙ። ብዙም ሳይቈይ ግን፣ “ሰሜናዊ ምሥራቅ” የሚሉት ኀይለኛ ዐውሎ ነፋስ ከደሴቲቱ ተነሥቶ ቍልቍል መጣባቸው። መርከቢቱም በማዕበሉ ስለ ተያዘች፣ ወደ ነፋሱ መግፋት አልቻለችም፤ ስለዚህ መንገድ ለቅቀን በነፋሱ ተነዳን። ቄዳ የተባለችውን ትንሽ ደሴት ተገን አድርገን በማለፍ፣ የመርከቧን ሕይወት አድን ጀልባ በብዙ ድካም ለማትረፍ ቻልን፤ ጀልባዋንም ወደ ላይ ጐትተው ካወጧት በኋላ መርከቧ እንዳትፈራርስ ዙሪያዋን በገመድ ጠምጥመው አሰሯት፤ ስርቲስ ከተባለው አሸዋማ ደለል ጋራ ሄደው እንዳይላተሙ ስለ ፈሩም፣ የመርከቧን ሸራ አውርደው እንዲሁ በዘፈቀደ እንድትነዳ አደረጉ። ማዕበሉም ክፉኛ ስላንገላታን፣ በማግስቱም ጭነቱን እያነሡ ወደ ባሕር ይጥሉ ጀመር፤ በሦስተኛውም ቀን፣ የመርከቧን ሸራ ማውጫና ማውረጃ መሣሪያ በገዛ እጃቸው ነቃቅለው ወደ ባሕር ጣሉት። ብዙ ቀን፣ ፀሓይንም ከዋክብትንም ማየት ስላልተቻለና ነፋስ ስለ በረታብን፣ ለመትረፍ የነበረን ተስፋ ሁሉ ተሟጠጠ። ሰዎቹ እህል ሳይቀምሱ ብዙ ቀን ከቈዩ በኋላ፣ ጳውሎስ በመካከላቸው ቆሞ እንዲህ አለ፤ “እናንተ ሰዎች ሆይ፤ የነገርኋችሁን ሰምታችሁ ቢሆን ኖሮ፣ ከቀርጤስ ባልተነሣችሁና ይህ ጕዳትና ጥፋት ባልደረሰባችሁ ነበር። አሁንም ቢሆን አይዟችሁ፤ መርከቧ እንጂ ከእናንተ አንዲት ነፍስ እንኳ አትጠፋምና። በትናንትናዋ ሌሊት፣ የርሱ የሆንሁትና የማመልከው እግዚአብሔር የላከው መልአክ በአጠገቤ ቆሞ፣ ‘ጳውሎስ ሆይ፤ አትፍራ፤ በቄሳር ፊት መቆም ይገባሃል፤ ከአንተ ጋራ የሚጓዙትንም ሰዎች ሕይወት እግዚአብሔር አትርፎልሃል’ አለኝ። ስለዚህ፣ እናንተ ሰዎች ሆይ፤ አይዟችሁ እርሱ እንደ ነገረኝ እንደዚያው እንደሚሆን በእግዚአብሔር አምናለሁና።
ሐዋርያት ሥራ 27 ያንብቡ
ያዳምጡ ሐዋርያት ሥራ 27
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሐዋርያት ሥራ 27:1-25
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች