ሐዋርያት ሥራ 27:1-25
ሐዋርያት ሥራ 27:1-25 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከዚህም በኋላ ፊስጦስ ወደ ቄሣር ወደ ኢጣልያ በመርከብ እንሄድ ዘንድ ባዘዘ ጊዜ ጳውሎስ ከሌሎች እስረኞች ጋር አብሮ የአውግስጦስ ጭፍራ ለነበረ ዩልዮስ ለሚባል የመቶ አለቃ ተሰጠ። በተነሣንም ጊዜ ወደ እስያ በምትሄድ በአድራማጢስ መርከብ ተሳፈርን፤ የተሰሎንቄ ሀገር ሰው የሚሆን መቄዶንያዊው አርስጥሮኮስም አብሮን ሄደ። በማግሥቱም ወደ ሲዶና ደረስን፤ ዩልዮስም ለጳውሎስ አዘነለት፤ ወደ ወዳጆቹ እንዲሄድና በእነርሱ ዘንድ እንዲያርፍም ፈቀደለት። ከዚያም ወጥተን ነፋስ ፊት ለፊት ነበርና በቆጵሮስ በኩል ዐለፍን። ወደ ኪልቅያና ወደ ጵንፍልያ ባሕርም ገብተን የሉቅያ ክፍል ወደምትሆነው ወደ ሙራ ሄድን። በዚያም የመቶ አለቃው ወደ ኢጣልያ የምትሄድ የእስክንድርያን መርከብ አገኘ፤ ወደ እርስዋም አስገባን። ብዙ ቀንም እያዘገምን ሄድን፤ በጭንቅም ወደ ቀኒዶስ አንጻር ደረስን፤ ወደዚያም በቀጥታ ለመድረስ ነፋስ ቢከለክለን በቀርጤስ በኩል በሰልሙና ፊት ለፊት ዐለፍን። ባጠገብዋም በጭንቅ ስናልፍ ላሲያ ለምትባለው ከተማ አቅራቢያ ወደ ሆነችው መልካም ወደብ ወደምትባለው ቦታ ደረስን። በዚያም ብዙ ቀን ቈየን፤ የአይሁድም የጾም ወራት አልፎ ስለ ነበረ በመርከብ ለመሄድ የሚያስፈራ ነበርና ጳውሎስ እንዲህ ብሎ መከራቸው። “እናንተ ሰዎች ሆይ፥ ስሙኝ፤ ጕዞአችን በብዙ ጭንቀትና በከባድ ጥፋት ላይ ሆኖ አያለሁ፤ ይህንም የምለው ጥፋቱ በራሳችንም ሕይወት እንጂ በጭነቱና በመርከቡ ብቻ ስላልሆነ ነው።” የመቶ አለቃው ግን ለመርከቡ ባለቤትና ለመሪው ይታዘዝ ነበር፤ የጳውሎስን ቃል ግን አይቀበልም ነበር። ያም ወደብ ክረምቱን ሊከርሙበት የማይመች ነበር፤ ስለዚህም ብዙዎች ከዚያ ይወጡ ዘንድ ይቻላቸው እንደ ሆነ በቀኝ በኩል ወደ አለው ፊንቄ ወደሚባለው ወደ ሁለተኛው የቀርጤስ ወደብ ይደርሱ ዘንድ ወደዱ። ልከኛ የአዜብ ነፋስም ነፈሰ፤ እነርሱም እንደ ወደዱ የሚደርሱ መስሎአቸው ነበር፤ መልሕቁንም አነሡ፤ በቀርጤስም አጠገብ ሄዱ። ከጥቂት ጊዜ በኋላም አውራቂስ የሚሉት ጽኑዕ ዓውሎ ነፋስ መጣ። መርከባችንም ተመትታ ተነጠቀች፤ ቀዛፊዎችም በነፋሱ ፊት ለፊት መቆም አልተቻላቸውምና ተዉአት፤ ብቻዋንም ሄደች። ከዚህም በኋላ ቄዳ ወደምትባል ደሴት እስክንገባ ድረስ ነፋሱ ነፈሰ፤ በጭንቅም ታንኳችንን ለመግታት ቻልን። ከዚህ በኋላ ተጋግዘን በገመድ አጠናከርናት፤ ከዚህም ቀጥሎ ቀዛፊዎች ወደ ጥልቁ ባሕር እንዳይወድቁ በፈሩ ጊዜ ሸራውን አወረዱ፤እንዲሁም እንድንሄድ አደረግን። በማግሥቱም ማዕበል ጸናብን፤ ከጭነቱም ወደ ባሕር ጣልን። በሦስተኛውም ቀን በመርከብ ያለውን ሁሉ በእጃችን እያነሣን በባሕር ላይ ጣልን። ብዙ ቀንም ፀሐይንና ጨረቃን ከዋክብትንም ሳናይ ማዕበሉ ጸናብን፤ ለመዳንም ተስፋ ቈርጠን ነበር። ከእኛም መብል የበላ አልነበረም። ጳውሎስም ተነሥቶ በመካከል ቆመና እንዲህ አላቸው፥ “እናንተ ሰዎች ሆይ፥ ቀድሞ ቃሌን ሰምታችሁኝ ቢሆን ከቀርጤስም ባትወጡ ኖሮ ከዚህ ጕዳትና መከራ በዳናችሁ ነበር። አሁንም እላችኋለሁ፤ መርከባችን እንጂ ከመካከላችን አንድ ሰው ስንኳ አይጠፋምና አትፍሩ። እኔ ለእርሱ የምሆንና የማመልከው እግዚአብሔር የላከው መልአክ በዚች ሌሊት በአጠገቤ ቆሞ ነበርና። እርሱም እንዲህ አለኝ፦ ‘ጳውሎስ ሆይ፥ አትፍራ፤ በቄሣር ፊት ልትቆም ይገባሃል፤ ከአንተም ጋር የሚሄዱትን ሁሉ እነሆ፥ እግዚአብሔር ለአንተ ሰጥቶሃል።’ አሁንም ወንድሞች ሆይ፥ ደስ ይበላችሁ፤ እንደ ነገረኝ እንደሚሆን በእግዚአብሔር አምናለሁና።
ሐዋርያት ሥራ 27:1-25 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ወደ ኢጣሊያ እንድንሄድ በተወሰነ ጊዜ፣ ጳውሎስንና ሌሎቹን እስረኞች የንጉሠ ነገሥቱ ክፍለ ጦር አባል ለሆነው፣ ዩልዮስ ለተባለ የመቶ አለቃ አስረከቧቸው። ከአድራሚጢስ ተነሥቶ በእስያ አውራጃ ባሕር ዳርቻ ላይ ወዳሉት ወደቦች በሚሄደው መርከብ ተሳፍረን የባሕር ጕዞ ጀመርን፤ በተሰሎንቄ ይኖር የነበረው የመቄዶንያ ሰው፣ አርስጥሮኮስም ከእኛ ጋራ ነበረ። በሚቀጥለው ቀን ሲዶና ደረስን፤ ዩልዮስም ለጳውሎስ ደግነት በማሳየት ወደ ወዳጆቹ ሄዶ ርዳታ እንዲቀበል ፈቀደለት። ከዚያም ተነሥተን በባሕር ተጓዝን፤ ነፋስ ከፊት ለፊት ስለ ገጠመን፣ የቆጵሮስን ደሴት ተገን አድርገን ዐለፍን። በኪልቅያና በጵንፍልያ ዳርቻ ያለውን ባሕር ከተሻገርን በኋላ በሉቅያ አገር ሙራ የተባለ ቦታ ደረስን። ከዚያም የመቶ አለቃው ወደ ኢጣሊያ የሚሄድ የእስክንድርያ መርከብ አግኝቶ አሳፈረን። ብዙ ቀን በዝግታ እየተጓዝን ቀኒዶስ አካባቢ በጭንቅ ደረስን፤ ነፋሱም ወደ ፊት እንዳንሄድ በከለከለን ጊዜ፣ በሰልሙና አጠገብ አድርገን በቀርጤስ ተተግነን ሄድን፤ ጥግ ጥጉንም ይዘን፣ በላሲያ ከተማ አጠገብ ወዳለው፣ “መልካም ወደብ” ወደ ተባለ ስፍራ በጭንቅ ደረስን። ብዙ ጊዜ ባክኖ፤ የጾሙ ጊዜ ስላለፈ በመርከብ መጓዙ አደገኛ ሆኖ ነበርና ጳውሎስ፣ “እናንተ ሰዎች፤ ጕዞው አደገኛ እንደሚሆን፣ በመርከቡና በጭነቱ እንዲሁም በእኛ በራሳችን ላይ እንኳ ትልቅ ጕዳት እንደሚደርስ ይታየኛል” ብሎ አስጠነቀቃቸው። የመቶ አለቃው ግን ከጳውሎስ ምክር ይልቅ የመርከቡ መሪና የመርከቡ ባለቤት ያሉትን ይሰማ ነበር። ክረምቱንም በዚያ ለማሳለፍ ወደቡ አመቺ ስላልነበረ፣ አብዛኛዎቹ ፍንቄ ወደተባለው ወደብ ደርሰው በዚያ ለመክረም ተስፋ በማድረግ ጕዟችንን እንድንቀጥል ውሳኔ አስተላለፉ፤ ወደቡም በቀርጤስ ደቡብ ምዕራብና ሰሜን ምዕራብ ትይዩ የሚገኝ ነበር። መጠነኛ የደቡብ ነፋስ በነፈሰ ጊዜም እንዳሰቡት የሆነላቸው መስሏቸው መልሕቁን ነቅለው፣ የቀርጤስን ዳርቻ በመያዝ ተጓዙ። ብዙም ሳይቈይ ግን፣ “ሰሜናዊ ምሥራቅ” የሚሉት ኀይለኛ ዐውሎ ነፋስ ከደሴቲቱ ተነሥቶ ቍልቍል መጣባቸው። መርከቢቱም በማዕበሉ ስለ ተያዘች፣ ወደ ነፋሱ መግፋት አልቻለችም፤ ስለዚህ መንገድ ለቅቀን በነፋሱ ተነዳን። ቄዳ የተባለችውን ትንሽ ደሴት ተገን አድርገን በማለፍ፣ የመርከቧን ሕይወት አድን ጀልባ በብዙ ድካም ለማትረፍ ቻልን፤ ጀልባዋንም ወደ ላይ ጐትተው ካወጧት በኋላ መርከቧ እንዳትፈራርስ ዙሪያዋን በገመድ ጠምጥመው አሰሯት፤ ስርቲስ ከተባለው አሸዋማ ደለል ጋራ ሄደው እንዳይላተሙ ስለ ፈሩም፣ የመርከቧን ሸራ አውርደው እንዲሁ በዘፈቀደ እንድትነዳ አደረጉ። ማዕበሉም ክፉኛ ስላንገላታን፣ በማግስቱም ጭነቱን እያነሡ ወደ ባሕር ይጥሉ ጀመር፤ በሦስተኛውም ቀን፣ የመርከቧን ሸራ ማውጫና ማውረጃ መሣሪያ በገዛ እጃቸው ነቃቅለው ወደ ባሕር ጣሉት። ብዙ ቀን፣ ፀሓይንም ከዋክብትንም ማየት ስላልተቻለና ነፋስ ስለ በረታብን፣ ለመትረፍ የነበረን ተስፋ ሁሉ ተሟጠጠ። ሰዎቹ እህል ሳይቀምሱ ብዙ ቀን ከቈዩ በኋላ፣ ጳውሎስ በመካከላቸው ቆሞ እንዲህ አለ፤ “እናንተ ሰዎች ሆይ፤ የነገርኋችሁን ሰምታችሁ ቢሆን ኖሮ፣ ከቀርጤስ ባልተነሣችሁና ይህ ጕዳትና ጥፋት ባልደረሰባችሁ ነበር። አሁንም ቢሆን አይዟችሁ፤ መርከቧ እንጂ ከእናንተ አንዲት ነፍስ እንኳ አትጠፋምና። በትናንትናዋ ሌሊት፣ የርሱ የሆንሁትና የማመልከው እግዚአብሔር የላከው መልአክ በአጠገቤ ቆሞ፣ ‘ጳውሎስ ሆይ፤ አትፍራ፤ በቄሳር ፊት መቆም ይገባሃል፤ ከአንተ ጋራ የሚጓዙትንም ሰዎች ሕይወት እግዚአብሔር አትርፎልሃል’ አለኝ። ስለዚህ፣ እናንተ ሰዎች ሆይ፤ አይዟችሁ እርሱ እንደ ነገረኝ እንደዚያው እንደሚሆን በእግዚአብሔር አምናለሁና።
ሐዋርያት ሥራ 27:1-25 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ወደ ኢጣሊያም በመርከብ እንሄድ ዘንድ በተቈረጠ ጊዜ፥ ጳውሎስንና ሌሎችን እስረኞች ከአውግስጦስ ጭፍራ ለነበረ ዩልዮስ ለሚሉት ለመቶ አለቃ አሳልፈው ሰጡአቸው። በእስያም ዳርቻ ወዳሉ ስፍራዎች ይሄድ ዘንድ ባለው በአድራሚጢስ መርከብ ገብተን ተነሣን፤ የመቄዶንያም ሰው የሆነ የተሰሎንቄው አርስጥሮኮስ ከእኛ ጋር ነበረ። በነገውም ወደ ሲዶና ስንደርስ ዩልዮስ ለጳውሎስ ቸርነት አድርጎ እርዳታቸውን ይቀበል ዘንድ ወደ ወዳጆቹ እንዲሄድ ፈቀደለት። ከዚያም ተነሥተን ነፋሱ ፊት ለፊት ነበረና በቆጵሮስ ተተግነን ሄድን፤ በኪልቅያና በጵንፍልያም አጠገብ ያለውን ባሕር ከተሻገርን በኋላ በሉቅያ ወዳለ ወደ ሙራ ደረስን። የመቶ አለቃውም በዚያ ወደ ኢጣሊያ የሚሄድ የእስክንድርያውን መርከብ አግኝቶ ወደ እርሱ አገባን። ብዙ ቀንም እያዘገምን ሄደን በጭንቅ ወደ ቀኒዶስ አንጻር ደረስን፤ ነፋስም ስለ ከለከለን በቀርጤስ ተተግነን በሰልሙና አንጻር ሄድን፤ በጭንቅም ጥግ ጥጉን አልፈን ለላሲያ ከተማ ወደ ቀረበች መልካም ወደብ ወደሚሉአት ስፍራ መጣን። ብዙ ጊዜም ካለፈ በኋላ፥ የጦም ወራት አሁን አልፎ ስለ ነበረ በመርከብ ለመሄድ አሁን የሚያስፈራ ነበርና ጳውሎስ፦ “እናንተ ሰዎች ሆይ፥ ይህ ጕዞ በጥፋትና በብዙ ጕዳት እንዲሆን አያለሁ፤ ጥፋቱም በገዛ ሕይወታችን ነው እንጂ በጭነቱና በመርከቡ ብቻ አይደለም” ብሎ መከራቸው። የመቶ አለቃው ግን ጳውሎስ ከተናገረው ይልቅ የመርከብ መሪውንና የመርከቡን ባለቤት ያምን ነበር። ያም ወደብ ይከርሙበት ዘንድ የማይመች ስለ ሆነ፥ የሚበዙቱ ቢቻላቸው በሰሜንና በደቡብ ምዕራብ ትይዩ ወዳለው ፍንቄ ወደሚሉት ወደ ቀርጤስ ወደብ ደርሰው ይከርሙ ዘንድ ከዚያ እንዲነሡ መከሩ። ልከኛም የደቡብ ነፋስ በነፈሰ ጊዜ፥ እንዳሰቡት የሆነላቸው መስሎአቸው ተነሡ በቀርጤስም አጠገብ ጥግ ጥጉን አለፉ። ነገር ግን እጅግ ሳይዘገይ አውራቂስ የሚሉት ዓውሎ ነፋስ ከዚያ ወረደባቸው፤ መርከቡም ተነጥቆ ነፋሱን ሲቃወም መሄድ ስላልቻለ ለቀነው ተነዳን። ቄዳ በሚሉአትም ደሴት በተተገንን ጊዜ ታንኳይቱን ለመግዛት በጭንቅ ቻልን፤ ወደ ላይም ካወጡአት በኋላ መርከቡን በገመድ አስታጥቀው አጸኑ፤ ስርቲስም ወደሚሉት ወደ አሸዋ እንዳይወድቁ ፈርተው ሸራውን አውርደው እንዲሁ ተነዱ። ነፋሱም በርትቶ ሲያስጨንቀን በማንግሥቱ ከጭነቱ ወደ ባሕር ይጥሉ ነበር፥ በሦስተኛውም ቀን የመርከቡን ዕቃ በእጃችን ወረወርን። ብዙ ቀንም ፀሐይን ከዋክብትንም ሳናይ ትልቅ ነፋስም ሲበረታብን ጊዜ፥ ወደ ፊት እንድናለን የማለት ተስፋ ሁሉ ተቈረጠ። ሳይበሉም ብዙ ቀን ከቆዩ በኋላ፥ ያን ጊዜ ጳውሎስ በመካከላቸው ቆሞ እንዲህ አለ፦ “እናንተ ሰዎች ሆይ፥ ሰምታችሁኝ በሆነ ኖሮ ከቀርጤስ እንዳትነሡ ይህንም ጥፋትና ጕዳት እንዳታገኙ ይገባችሁ ነበር። አሁንም፦ አይዞአችሁ ብዬ እመክራችኋለሁ፤ ይህ መርከብ እንጂ ከእናንተ አንድ ነፍስ እንኳ አይጠፋምና። የእርሱ የምሆንና ደግሞ የማመልከው የእግዚአብሔር መልአክ በዚች ሌሊት በአጠገቤ ቆሞ ነበርና፥ እርሱም፦ “ጳውሎስ ሆይ፥ አትፍራ፤ በቄሣር ፊት ልትቆም ይገባሃል፤ እነሆም፥ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር የሚሄዱትን ሁሉ ሰጥቶሃል” አለኝ። ስለዚህ እናንተ ሰዎች ሆይ፥ አይዞአችሁ፤ እንደ ተናገረኝ እንዲሁ እንዲሆን እግዚአብሔርን አምናለሁ።
ሐዋርያት ሥራ 27:1-25 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ወደ ኢጣሊያ በመርከብ እንድንሄድ በተወሰነ ጊዜ ጳውሎስንና ሌሎችንም እስረኞች በአውግስጦስ ክፍለ ጦር ውስጥ ለነበረው ዩልዮስ ለሚባለው መቶ አለቃ አስረከቡአቸው። በእስያ የባሕር ዳርቻ ወዳሉት ወደቦች በሚሄደው የአድራሚጥዮን መርከብ ተሳፍረን ተጓዝን፤ በተሰሎንቄ የሚኖረው የመቄዶንያው ሰው አርስጥሮኮስም ከእኛ ጋር ነበረ። በማግስቱ ወደ ሲዶና ደረስን፤ ዩልዮስ ለጳውሎስ ደግ ስለ ነበረ ወደ ወዳጆቹ ሄዶ የሚያስፈልገውን ርዳታ እንዲያደርጉለት ፈቀደለት። ከዚያም ተነሥተን ነፋሱ ከፊት ለፊት ይነፍስብን ስለ ነበር የቆጵሮስን ደሴት ተገን አድርገን በመርከብ ጒዞአችንን ቀጠልን። በኪልቅያና በጵንፍልያ አጠገብ ያለውን ባሕር ከተሻገርን በኋላ በሊቅያ አገር ወዳለው ወደ ሙራ ከተማ ደረስን። እዚያ የመቶ አለቃው ወደ ኢጣሊያ የሚሄድ የእስክንድርያ መርከብ አገኘና በእርሱ ላይ እንድንሳፈር አደረገ። ብዙ ቀን ቀስ እያልን ተጒዘን በብዙ ችግር ወደ ቀኒዶስ ከተማ አጠገብ ደረስን፤ ነፋሱም ወደፊት እንዳንሄድ ስለ ከለከለን በሰልሞና ርእሰ ምድር ጫፍ አጠገብ አለፍንና የቀርጤስን ደሴት ተገን አድርገን ሄድን። በብዙ ችግር ጥግ ጥጉን ካለፍን በኋላ በላስያ ከተማ አጠገብ ወደምትገኘው “መልካም ወደብ” ወደምትባለው ስፍራ ደረስን። በጒዞአችን ላይ ብዙ ጊዜ በመባከኑና የጾም ጊዜ በማለፉ ምክንያት በዚህ ጊዜ በባሕር ላይ መጓዝ አደገኛ ስለ ነበር ጳውሎስ ለሰዎቹ እንዲህ ሲል አስጠነቀቃቸው፤ “እናንተ ሰዎች! ከእንግዲህ ወዲህ ያለው ጒዞአችን አደጋ እንዳለበት ይታየኛል፤ በጭነቱና በመርከቡ ላይ ብቻ ሳይሆን በሰው ሕይወትም ላይ ብርቱ ጒዳትና ጥፋት ይደርሳል።” የመቶ አለቃው ግን ከጳውሎስ ምክር ይልቅ የመርከቡ አዛዥና የመርከቡ ባለቤት የሚሉትን ይሰማ ነበር። ያ ወደብ ለክረምት ማሳለፊያ ምቹ ስላልነበረ አብዛኞቹ ሰዎች “ጒዞአቸውን ቀጥለው የሚቻል ቢሆን በሰሜን ምዕራብና በደቡብ ምዕራብ በር ወዳለው ፊንቄ ወደሚባለው የቀርጤስ ወደብ ደርሰን ክረምቱን እዚያ እናሳልፍ” ብለው አሳብ አቀረቡ። አነስተኛ የደቡብ ነፋስ ሲነፍስ ባዩ ጊዜ እንዳሰቡት የሆነላቸው መስሎአቸው መልሕቃቸውን አንሥተው ጒዞአቸውን ለመቀጠል ተነሡ፤ ከወደቡም ተነሥተው በቀርጤስ አጠገብ አድርገው ጥግ ጥጉን አለፉ። ነገር ግን ከጥቂት ጊዜ በኋላ “የሰሜናዊ ምሥራቅ ዐውሎ ነፋስ” የሚባል ኀይለኛ ነፋስ ከደሴቲቱ ተነሥቶ ወደ ባሕሩ መጣባቸው። መርከቡም ስለ ተገፋና ነፋሱን መቋቋም ስላልቻለ ዝም ብለን በነፋሱ እየተነዳን ሄድን። ቄዳ የተባለችውን ደሴት ተገን አድርገን ስንጓዝ በታላቅ ችግር የመርከቡን ጀልባ ይዘን በቊጥጥራችን ሥር ለማድረግ ቻልን። መርከበኞቹ ጀልባውን ወደ መርከቡ ስበው ካወጡት በኋላ በመርከቡ ዙሪያ ገመድ ጠመጠሙ፤ መርከቡ ሱርቲስ ወደምትባል አሸዋማ ስፍራ እንዳይወድቅ ፈርተው ሸራውን አወረዱና በነፋስ እየተነዱ ሄዱ። ዐውሎ ነፋሱ እየበረታብን ስለ ሄደ በማግስቱ በመርከቡ ላይ ከተጫኑት ዕቃዎች እያንዳንዱን ወደ ባሕር መጣል ጀመሩ። በሦስተኛውም ቀን ለመርከቡ የሚያገለግሉትን ዕቃዎች በገዛ እጃቸው እየወረወሩ ጣሉ፤ ለብዙ ቀን ፀሐይም ሆነ፤ ከዋክብት ስላልታዩና ነፋሱም እየበረታብን ስለ ሄደ ከእንግዲህ ወዲህ መዳን አንችልም ብለን ተስፋ ቈረጥን። ሰዎቹ ምንም ምግብ ሳይበሉ ብዙ ቀን ቈዩ፤ ስለዚህ ጳውሎስ በመካከላቸው ቆሞ እንዲህ አለ፦ “እናንተ ሰዎች! እኔ ያልኳችሁን ሰምታችሁ ከቀርጤስ ባትነሡ ኖሮ ይህ ሁሉ ጒዳትና ጥፋት ባልደረሰባችሁም ነበር። አሁንም መርከቡ ብቻ ይጐዳል እንጂ ከእናንተ በማንም ላይ ጥፋት አይደርስም፤ ስለዚህ አይዞአችሁ፤ አትፍሩ! ብዬ እመክራችኋለሁ። ባለፈው ሌሊት የእርሱ የሆንኩ የማመልከው አምላክ የላከው መልአክ በአጠገቤ ቆሞ ‘ጳውሎስ ሆይ! አትፍራ! በሮም ንጉሠ ነገሥት ፊት መቆም ይገባሃል! እነሆ፥ ከአንተ ጋር የሚጓዙትንም ሁሉ እግዚአብሔር ለአንተ ብሎ ከሞት ያድናቸዋል’ ብሎ ነግሮኛል። ስለዚህ እናንተ ሰዎች አይዞአችሁ! እግዚአብሔር ይህንን የነገረኝን ሙሉ በሙሉ እንደሚፈጽም አምነዋለሁ።
ሐዋርያት ሥራ 27:1-25 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ወደ ኢጣሊያም በመርከብ እንሄድ ዘንድ በተቆረጠ ጊዜ፥ ጳውሎስንና ሌሎችን እስረኞች ከአውግስጦስ ጭፍራ ለነበረ ዩልዮስ ለሚሉት ለመቶ አለቃ አሳልፈው ሰጡአቸው። በእስያም ዳርቻ ወዳሉ ስፍራዎች ይሄድ ዘንድ ባለው በአድራሚጢስ መርከብ ገብተን ተነሣን፤ የመቄዶንያም ሰው የሆነ የተሰሎንቄው አርስጥሮኮስ ከእኛ ጋር ነበረ። በነገውም ወደ ሲዶና ስንደርስ ዩልዮስ ለጳውሎስ ቸርነት አድርጎ እርዳታቸውን ይቀበል ዘንድ ወደ ወዳጆቹ እንዲሄድ ፈቀደለት። ከዚያም ተነሥተን ነፋሱ ፊት ለፊት ነበረና በቆጵሮስ ተተግነን ሄድን፤ በኪልቅያና በጵንፍልያም አጠገብ ያለውን ባሕር ከተሻገርን በኋላ በሉቅያ ወዳለ ወደ ሙራ ደረስን። የመቶ አለቃውም በዚያ ወደ ኢጣሊያ የሚሄድ የእስክንድርያውን መርከብ አግኝቶ ወደ እርሱ አገባን። ብዙ ቀንም እያዘገምን ሄደን በጭንቅ ወደ ቀኒዶስ አንጻር ደረስን፤ ነፋስም ስለ ከለከለን በቀርጤስ ተተግነን በሰልሙና አንጻር ሄድን፤ በጭንቅም ጥግ ጥጉን አልፈን ለላሲያ ከተማ ወደ ቀረበች መልካም ወደብ ወደሚሉአት ስፍራ መጣን። ብዙ ጊዜም ካለፈ በኋላ፥ የፆም ወራት አሁን አልፎ ስለ ነበረ በመርከብ ለመሄድ አሁን የሚያስፈራ ነበርና ጳውሎስ “እናንተ ሰዎች ሆይ! ይህ ጉዞ በጥፋትና በብዙ ጉዳት እንዲሆን አያለሁ፤ ጥፋቱም በገዛ ሕይወታችን ነው እንጂ በጭነቱና በመርከቡ ብቻ አይደለም፤” ብሎ መከራቸው። የመቶ አለቃው ግን ጳውሎስ ከተናገረው ይልቅ የመርከብ መሪውንና የመርከቡን ባለቤት ያምን ነበር። ያም ወደብ ይከርሙበት ዘንድ የማይመች ስለ ሆነ፥ የሚበዙቱ ቢቻላቸው በሰሜንና በደቡብ ምዕራብ ትይዩ ወዳለው ፍንቄ ወደሚሉት ወደ ቀርጤስ ወደብ ደርሰው ይከርሙ ዘንድ ከዚያ እንዲነሡ መከሩ። ልከኛም የደቡብ ነፋስ በነፈሰ ጊዜ፥ እንዳሰቡት የሆነላቸው መስሎአቸው ተነሡ፤ በቀርጤስም አጠገብ ጥግ ጥጉን አለፉ። ነገር ግን እጅግ ሳይዘገይ አውራቂስ የሚሉት ዓውሎ ነፋስ ከዚያ ወረደባቸው፤ መርከቡም ተነጥቆ ነፋሱን ሲቃወም መሄድ ስላልቻለ ለቀነው ተነዳን። ቄዳ በሚሉአትም ደሴት በተተገንን ጊዜ ታንኳይቱን ለመግታት በጭንቅ ቻልን፤ ወደ ላይም ካወጡአት በኋላ መርከቡን በገመድ አስታጥቀው አጸኑ፤ ስርቲስም ወደሚሉት ወደ አሸዋ እንዳይወድቁ ፈርተው ሸራውን አውርደው እንዲሁ ተነዱ። ነፋሱም በርትቶ ሲያስጨንቀን በማንግሥቱ ከጭነቱ ወደ ባሕር ይጥሉ ነበር፤ በሦስተኛውም ቀን የመርከቡን ዕቃ በእጃችን ወረወርን። ብዙ ቀንም ፀሐይን ከዋክብትንም ሳናይ ትልቅ ነፋስም ሲበረታብን ጊዜ፥ ወደ ፊት እንድናለን የማለት ተስፋ ሁሉ ተቆረጠ። ሳይበሉም ብዙ ቀን ከቆዩ በኋላ፥ ያንጊዜ ጳውሎስ በመካከላቸው ቆሞ እንዲህ አለ “እናንተ ሰዎች ሆይ! ሰምታችሁኝ በሆነ ኖሮ ከቀርጤስ እንዳትነሡ ይህንም ጥፋትና ጉዳት እንዳታገኙ ይገባችሁ ነበር። አሁንም አይዞአችሁ ብዬ እመክራችኋለሁ፤ ይህ መርከብ እንጂ ከእናንተ አንድ ነፍስ እንኳ አይጠፋምና። የእርሱ የምሆንና ደግሞ የማመልከው የእግዚአብሔር መልአክ በዚች ሌሊት በአጠገቤ ቆሞ ነበርና፤ እርሱም ጳውሎስ ሆይ! አትፍራ፤ በቄሣር ፊት ልትቆም ይገባሃል፤ እነሆም፥ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር የሚሄዱትን ሁሉ ሰጥቶሃል፤” አለኝ። ስለዚህ እናንተ ሰዎች ሆይ! አይዞአችሁ፤ እንደ ተናገረኝ እንዲሁ እንዲሆን እግዚአብሔርን አምናለሁ።