ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 18
18
1ዳዊትም ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሕዝብ ቈጠረ፥ ሻለቆችንና የመቶ አለቆችንም ሾመላቸው። 2ዳዊትም ሕዝቡን ከኢዮአብ እጅ በታች ሢሶውን፥ ከኢዮአብም ወንድም ከጽሩያ ልጅ ከአቢሳ እጅ በታች ሢሶውን፥ ከጌት ሰውም ከኢታይ እጅ በታች ሢሶውን ሰደደ። ንጉሡም ሕዝቡን፦ እኔ ደግሞ ከእናንተ ጋር እወጣለሁ አላቸው። 3ሕዝቡ ግን፦ አትወጣም፥ ብንሸሽ ስለ እኛ አያስቡም፥ ከእኛም እኩሌታው ቢሞት ስለ እኛ አያስቡም፥ አንተ ግን ለብቻህ ከእኛ ከአሥሩ ሺህ ይልቅ ትበልጣለህ፥ አሁንም በከተማ ተቀምጠህ ብትረዳን ይሻላል አሉ። 4ንጉሡም፦ መልካም የሚመስላችሁን አደርጋለሁ አላቸው። ንጉሡም በበሩ አጠገብ ቆመ፥ ሕዝቡም ሁሉ መቶ በመቶ ሺህ በሺህ እየሆኑ ወጡ። 5ንጉሡም ኢዮአብንና አቢሳን ኢታይንም፦ ለብላቴናው ለአቤሴሎም ስለ እኔ ራሩለት ብሎ አዘዛቸው። ንጉሡም ስለ አቤሴሎም አለቆቹን ሁሉ ሲያዝዝ ሕዝቡ ሁሉ ሰማ። 6ሕዝቡም በእስራኤል ላይ ወደ ሜዳ ወጣ፥ ሰልፉም በኤፍሬም ዱር ውስጥ ሆነ። 7በዚያም የእስራኤል ሕዝብ በዳዊት ባሪያዎች ፊት ተመቱ፥ በዚያም ቀን ታላቅ ውጊያ በዚያ ሆነ፥ ሀያ ሺህ ሰውም ሞተ። 8ከዚያም ሰልፉ በአገሩ ሁሉ ፊት ላይ ተበተነ፥ በዚያም ቀን ሰይፍ ከዋጠው ሕዝብ ይልቅ ዱር ብዙ ዋጠ። 9አቤሴሎም ከዳዊት ባሪያዎች ጋር በድንገት ተገናኘ፥ አቤሴሎምም በበቅሎ ተቀምጦ ነበር፥ በቅሎውም ብዙ ቅርንጫፍ ባለው በታላቅ ዛፍ በታች ገባ፥ ራሱም በዛፉ ተያዘ፥ በሰማይና በምድር መካከል ተንጠለጠለ፥ ተቀምጦበትም የነበረ በቅሎ አለፈ። 10አንድ ሰውም አይቶ፦ እነሆ፥ አቤሴሎም በትልቅ ዛፍ ላይ ተንጠልጥሎ አየሁ ብሎ ለኢዮአብ ነገረው። 11ኢዮአብም ለነገረው ሰው፦ እነሆ፥ ካየኸው ለምን ወደ ምድር አልመታኸውም? አሥር ብርና አንድ ድግ እሰጥህ ነበር አለው። 12ሰውዮውም ኢዮአብን፦ እኛ ስንሰማ ንጉሡ አንተንና አቢሳን ኢታይንም፦ ብላቴናውን አቤሴሎምን ማንም እንዳይነካው ተጠንቀቁ ብሎ አዝዞአልና ሺህ ብር በእጄ ላይ ብትመዝን እጄን በንጉሡ ልጅ ላይ ባልዘረጋሁም ነበር አለው። 13እኔ ቅሉ በነፍሱ ላይ ብወነጅል ኖሮ ይህ ከንጉሥ ባልተሰወረም፥ አንተም በተነሣህብኝ ነበር አለው። 14ኢዮአብም፦ እኔ ከአንተ ጋር እንዲህ እዘገይ ዘንድ አልችልም ብሎ ሦስት ጦሮች በእጁ ወሰደ፥ አቤሴሎምም ገና በዛፍ ላይ ተንጠልጥሎ ሕያው ሳለ በልቡ ላይ ተከላቸው። 15አሥሩም የኢዮአብ ጋሻ ጃግሬዎች ከበቡት፥ አቤሴሎምንም መትተው ገደሉት። 16ኢዮአብም ሕዝቡን ከልክሎ ነበርና ቀንደ መለከት ነፋ፥ ሕዝቡም እስራኤልን ከማሳደድ ተመለሰ። 17አቤሴሎምንም ወስደው በዱር ባለ በታላቅ ጕድጓድ ውስጥ ጣሉት፥ እጅግም ታላቅ የሆነ የድንጋይ ክምር ከመሩበት፥ እስራኤልም ሁሉ እያንዳንዱ ወደ ድንኳኑ ሸሸ። 18አቤሴሎምም ሕያው ሳለ፦ ለስሜ መታሰቢያ የሚሆን ልጅ የለኝም ብሎ ሐውልት ወስዶ በንጉሥ ሸለቆ ውስጥ ለራሱ አቁሞ ነበር፥ ሐውልቱንም በስሙ ጠርቶት ነበር፥ እስከ ዛሬም ድረስ የአቤሴሎም መታሰቢያ ተብሎ ይጠራል። 19የሳዶቅ ልጅ አኪማአስ ግን፦ እግዚአብሔር ጠላቶቹን እንደተበቀለለት ሮጬ ለንጉሥ የምሥራች ልንገር አለ። 20ኢዮአብም፦ በሌላ ቀን እንጂ ዛሬ ወሬ አትናገርም፥ የንጉሥ ልጅ ሞቶአልና ዛሬ ወሬ አትናገርም አለው። 21ኢዮአብም ኵሲን፦ ሂድ ያየኸውንም ለንጉሡ ንገር አለው። ኵሲም ለኢዮአብ እጅ ነሥቶ ሮጠ። 22ዳግመኛም የሳዶቅ ልጅ አኪማአስ ኢዮአብን፦ የሆነ ሆኖ ኵሲን ተከትዬ፥ እባክህ፥ ልሩጥ አለው። ኢዮአብም፦ ልጄ ሆይ፥ መልካም ወሬ የምትወስድ አይደለህምና ትሮጥ ዘንድ ለምን ትወድዳለህ? አለ። 23እርሱም፦ እኔ ብሮጥ ምን ይገድዳል? አለ። እርሱም፦ ሩጥ አለው። አኪማአስም በሜዳው መንገድ በኩል ሮጠ፥ ኵሲንም ቀደመው። 24ዳዊትም በሁለት በር መካከል ተቀምጦ ነበር፥ ዘበኛውም በቅጥሩ ላይ ወዳለው ወደበሩ ሰገነት ወጣ፥ አይኑንም አቅንቶ ብቻውን የሚሮጥ ሰው አየ። 25ዘበኛውም ለንጉሡ ሊነግረው ጮኸ። ንጉሡም፦ ብቻውን እንደሆነ በአፉ ወሬ ይኖራል አለ። 26እርሱም ፈጥኖ ቀረበ። ዘበኛውም ሌላ ሰው ሲሮጥ አየ፥ ዘበኛውም ለደጅ ጠባቂው ጮኾ፦ እነሆ፥ ብቻውን የሚሮጥ ሌላ ሰው አየሁ አለ። ንጉሡም፦ እርሱ ደግሞ ወሬ ይዞ ይሆናል አለ። 27ዘበኛውም፦ የፊተኛው ሩጫ እንደ ሳዶቅ ልጅ እንደ አኪማአስ ሩጫ ይመስላል አለ፥ ንጉሡም እርሱ መልካም ሰው ነው፥ መልካም ወሬ ያመጣል አለ። 28አኪማአስም ጮኾ ንጉሡን፦ ሁሉ ደህና ሆኖአል አለው። በንጉሡም ፊት በምድር ላይ በግንባሩ ተደፍቶ፦ በንጉሡ በጌታዬ ላይ እጃቸውን ያነሡትን ሰዎች አሳልፎ የሰጠ አምላክህ እግዚአብሔር ይመስገን አለ። 29ንጉሡም፦ ብላቴናው አቤሴሎም ደህና ነውን? አለ። አኪማአስም፦ ኢዮአብ እኔን ባሪያህንና የንጉሡን ባሪያ በላከ ጊዜ ትልቅ ሽብር አይቻለሁ፥ ምን እንደሆነ ግን አላወቅሁም ብሎ መለሰለት። 30ንጉሡም፦ ፈቀቅ ብለህ ቁም አለ፥ እርሱም ፈቀቅ ብሎ ቆመ። 31እነሆም፥ ኵሲ መጣ፥ ኵሲም፦ እግዚአብሔር በላይህ የተነሡትን ሁሉ ዛሬ እንደ ተበቀለልህ ለጌታዬ ለንጉሡ ወሬ አምጥቼአለሁ አለ። 32ንጉሡም ኵሲን፦ ብላቴናው አቤሴሎም ደኅና ነውን? አለው። ኵሲም፦ የጌታዬ የንጉሡ ጠላቶች፥ በክፉም የተነሡብህ ሁሉ እንደዚያ ብላቴና ይሁኑ ብሎ መለሰለት። 33ንጉሡም እጅግ አዘነ፥ በበሩም ላይ ወዳለችው ቤት ወጥቶ አለቀሰ፥ ሲሄድም፦ ልጄ አቤሴሎም ሆይ፥ ልጄ፥ ልጄ አቤሴሎም ሆይ፥ በአንተ ፋንታ ሞቼ ኖሮ ቢሆን፥ ልጄ አቤሴሎም፥ ልጄ ሆይ ይል ነበር።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 18: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ