የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 13

13
1ከዚህም በኋላ እንዲህ ሆነ፥ ለዳዊት ልጅ ለአቤሴሎም አንዲት የተዋበች እኅት ነበረችው፥ ስምዋም ትዕማር ነበረ፥ የዳዊት ልጅ አምኖን ወደዳት። 2አምኖንም ከእኅቱ ከትዕማር የተነሣ እጅግ ስለ ተከዘ ታመመ፥ ድንግልም ነበረችና አንዳች ያደርጋት ዘንድ በዓይኑ ፊት ጭንቅ ሆኖበት ነበር። 3ለአምኖንም የዳዊት ወንድም የሳምዓ ልጅ ኢዮናዳብ የሚባል ወዳጅ ነበረው፥ ኢዮናዳብም እጅግ ብልህ ሰው ነበረ። 4እርሱም፦ የንጉሥ ልጅ ሆይ፥ ስለ ምን ቀን በቀን እንዲህ ከሳህ? አትነግረኝምን? አለው። አምኖንም፦ የወንድሜን የአቤሴሎምን እኅት ትዕማርን እወድዳታለሁ አለው። 5ኢዮናዳብም፦ ታምሜአለሁ ብለህ በአልጋህ ላይ ተኛ፥ አባትህም ሊያይህ በመጣ ጊዜ፦ እኅቴ ትዕማር እንድትመጣና እኔ የምበላውን እንጀራ እንድትሰጠኝ፥ መብሉንም እኔ እያየሁ እንድታዘጋጅልኝ፥ ከእጅዋም እንድበላው እለምንሃለሁ በል አለው። 6እንዲሁም አምኖን፦ ታምሜአለሁ ብሎ ተኛ፥ ንጉሡም ሊያየው በመጣ ጊዜ አምኖን ንጉሡን፦ እኅቴ ትዕማር እንድትመጣና እኔ እያየሁ ሁለት እንጎቻ እንድታደርግልኝ፥ ከእጅዋም እንድበላ እለምንሃለሁ አለው።
7ዳዊትም፦ መብልን ታዘጋጂለት ዘንድ ወደ ወንድምሽ ወደ አምኖን ቤት ሂጂ ብሎ መልእክተኞችን ወደ ትዕማር ቤት ላከ። 8ትዕማርም ወደ ወንድምዋ ወደ አምኖን ቤት ሄደች፥ ተኝቶም ነበር፥ ዱቄትም ወስዳ ለወሰች፥ እያየም እንጎቻ አደረገች፥ ጋገረችም። 9ምጣዱንም ወስዳ በፊቱ ገለበጠች እርሱ ግን ይበላ ዘንድ እንቢ አለ። አምኖንም፦ ሰውን ሁሉ ከእኔ ዘንድ አስወጡ አለ፥ ሰውም ሁሉ ከእርሱ ዘንድ ወጣ። 10አምኖንም ትዕማርን፦ ከእጅሽ እበላ ዘንድ መብሉን ወደ እልፍኙ አግቢው አላት፥ ትዕማርም የሠራችውን እንጎቻ ወስዳ ወንድምዋ አምኖን ወዳለበት እልፍኝ አገባችው። 11መብሉንም ባቀረበች ጊዜ ያዛትና፦ እኅቴ ሆይ፥ ነዪ ከእኔም ጋር ተኚ አላት። 12እርስዋ መልሳ፦ ወንድሜ ሆይ፥ አይሆንም፥ እንዲህ ያለ ነገር በእስራኤል ዘንድ አይገባምና አታሳፍረኝ፥ ይህንም ነውረኛ ሥራ አታድርግ። 13እኔም ነውሬን ወዴት ልሸከም? አንተም በእስራኤል ዘንድ ከምናምንቴዎች እንደ አንዱ ትሆናለህ፥ እንግዲህስ ለንጉሡ ንገረው፥ እኔንም አይነሣህም አለችው። 14ቃልዋን ግን አልሰማም፥ ከእርስዋ ይልቅ ብርቱ ነበረና በግድ አስነወራት፥ ከእርስዋም ጋር ተኛ።
15ከዚያም በኋላ አምኖን ፈጽሞ ጠላት፥ አስቀድሞም ከወደዳት ውድ ይልቅ በኋላ የጠላት ጥል በለጠ። አምኖንም፦ ተነሥተሽ ሂጂ አላት። 16እርስዋም፦ አይሆንም፥ ቀድሞ ከሠራኸው ክፋት ይልቅ እኔን በማውጣትህ የበለጠ ክፋት ትሠራለህ አለችው፥ እርሱ ግን አልሰማትም። 17የሚያገለግለውንም ብላቴና ጠርቶ፦ ይህችን ሴት ከፊቴ አስወጥተህ በሩን ዝጋባት አለው። 18ብዙ ኅብር ያለውንም ልብስ ለብሳ ነበር፥ እንዲህ ያለውን ልብስ የንጉሡ ልጆች ደናግሉ ይለብሱ ነበርና፥ አገልጋዩም አስወጥቶ በሩን ዘጋባት። 19ትዕማርም በራስዋ ላይ አመድ ነስንሳ፥ ብዙ ኅብርም ያለውን ልብስዋን ተርትራ፥ እጅዋንም በራስዋ ላይ ጭና እየጮኸች ሄደች።
20ወንድምዋም አቤሴሎም፦ ወንድምሽ አምኖን ከአንቺ ጋር ነበረን? እኅቴ ሆይ፥ አሁን ግን ዝም በዪ፥ ወንድምሽ ነው፥ ይህን ነገር በልብሽ አትያዢው አላት። ትዕማርም በወንድምዋ በአቤሴሎም ቤት ብቻዋን ተቀመጠች። 21ንጉሡም ዳዊት ይህን ነገር ሁሉ በሰማ ጊዜ እጅግ ተቆጣ፥ ነገር ግን የበኵር ልጁ ነበረና ስለ ወደደው የልጁን የአምኖን ነፍስ አላሳዘነም። 22አቤሴሎምም እኅቱን ትዕማርን ስላሳፈራት አምኖንን ጠልቶታልና አቤሴሎም አምኖንን ክፉም ሆነ መልካምም አልተናገረውም።
23ከሁለት ዓመትም በኋላ አቤሴሎም በኤፍሬም አቅራቢያ ባለችው በቤላሶር በጎቹን አሸለተ፥ አቤሴሎምም የንጉሡን ልጆች ሁሉ ጠራ። 24አቤሴሎምም ወደ ንጉሡ መጥቶ፦ እነሆ፥ ባሪያህ በጎቹን ያሸልታል፥ ንጉሡና ሎሌዎቹ ከባሪያህ ጋር ይሂዱ አለው። 25ንጉሡም አቤሴሎምን፥ ልጄ ሆይ፥ እንከብድብሃለንና ሁላችን እንመጣ ዘንድ አይሆንም አለው። የግድም አለው፥ እርሱ ግን መረቀው እንጂ ለመሄድ እንቢ አለ። 26አቤሴሎምም አንተ እንቢ ካልህ ወንድሜ አምኖን ከእኛ ጋር እንዲሄድ እለምንሃለሁ አለ። ንጉሡም፦ ከአንተ ጋር ለምን ይሄዳል? አለው። 27አቤሴሎምም የግድ አለው፥ አምኖንንና የንጉሡንም ልጆች ሁሉ ከእርሱ ጋር ሰደደ። 28አቤሴሎምም እንደ ንጉሥ ግብዣ ያለ ግብዣ አደረገ፥ አቤሴሎምም አገልጋዮቹን፦ አምኖን የወይን ጠጅ ጠጥቶ ልቡን ደስ ባለው ጊዜ እዩ፦ አምኖንን ግደሉ ባልኋችሁም ጊዜ ግደሉት፥ አትፍሩም፥ ያዘዝኋችሁም እኔ ነኝና በርቱ ጽኑም ብሎ አዘዛቸው። 29የአቤሴሎምም አገልጋዮች አቤሴሎም እንዳዘዛቸው በአምኖን ላይ አደረጉበት። የንጉሡም ልጆች ሁሉ ተነሥተው በየበቅሎቻቸው ተቀምጠው ሸሹ።
30ገናም በመንገድ ሲሄዱ ለዳዊት፦ አቤሴሎም የንጉሡን ልጆች ሁሉ ገድሎአል፥ ከእነርሱም አንድ አልቀረም የሚል ወሬ መጣለት። 31ንጉሡም ተነሥቶ ልብሱን ቀደደ፥ በምድር ላይም ወደቀ፥ ባሪያዎቹም ሁሉ ልብሳቸውን ቀድደው በአጠገቡ ቆሙ። 32የዳዊትም ወንድም የሳምዓ ልጅ ኢዮናዳብ፦ ጌታዬ ጕልማሶቹ የንጉሡ ልጆች ሁሉ እንደ ሞቱ አያስብ፥ እኅቱን ትዕማርን በግድ ካስነወራት ጀምሮ በአቤሴሎም ዘንድ የተቆረጠ ነገር ነበረና የሞተ አምኖን ብቻ ነው። 33አሁንም የሞተ ብቻ ነው እንጂ የንጉሥ ልጆች ሁሉ ሞቱ ብሎ ጌታዬ ንጉሡ ይህን ነገር በልቡ አያኑር አለው።
34አቤሴሎምም ኮበለለ። ጕበኛውም ጕልማሳ ዓይኑን ከፍ አደረገ፥ እነሆም፥ ብዙ ሰዎች በኋላው በተራራው አጠገብ በመንገድ ሲመጡ አየ። 35ኢዮናዳብም ንጉሡን፦ እነሆ፥ የንጉሡ ልጆች መጥተዋል፥ ባሪያህ እንዳለው እንዲሁ ሆኖአል አለው። 36ተናግሮም በጨረሰ ጊዜ፥ እነሆ፥ ወዲያው የንጉሥ ልጆች ገቡ፥ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው አለቀሱ፥ ደግሞ ንጉሡና ባሪያዎቹ ሁሉ እጅግ ታላቅ ልቅሶ አለቀሱ።
37አቤሴሎም ግን ኮብልሎ ወደ ጌሹር ንጉሥ ወደ ዓሚሁድ ልጅ ወደ ተልማይ ሄደ። ዳዊትም ሁልጊዜ ለልጁ ያለቅስ ነበር። 38አቤሴሎም ኮብልሎ ወደ ጌሹር ሄደ፥ በዚያም ሦስት ዓመት ያህል ተቀመጠ። 39ንጉሡም ዳዊት ስለ አምኖን ሞት ተጽናንቶ ወደ አቤሴሎም ይሄድ ዘንድ እጅግ ናፈቀ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ