የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 3

3
በእስራኤልና በሞዓብ መካከል የተደረገ ጦርነት
1በይሁዳም ንጉሥ በኢዮሣፍጥ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በእስራኤል ላይ በሰማርያ መንገሥ ጀመረ፤ ዐሥራ ሁለት ዓመትም ነገሠ። 2በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ አደረገ፤ ነገር ግን አባቱ ያሠራውን የበኣልን ሐውልት አርቆአልና እንደ አባቱና እንደ እናቱ አልነበረም። 3ነገር ግን እስራኤልን ባሳታቸው በናባጥ ልጅ በኢዮርብዓም ኀጢአት ተያዘ፤ ከእርሱም አልራቀም።
4የሞዓብም ንጉሥ ሞሳ በግ አርቢ ነበረ፤ ለእስራኤልም ንጉሥ የመቶ ሺህ ጠቦትና የመቶ ሺህ አውራ በጎች ጠጕር ይገብርለት ነበር። 5አክዓብም ከሞተ በኋላ የሞዓብ ንጉሥ በእስራኤል ንጉሥ ላይ ዐመፀ። 6በዚያም ጊዜ ንጉሡ ኢዮራም ከሰማርያ ወጥቶ እስራኤልን ሁሉ አሰለፈ። 7ወደ ይሁዳም ንጉሥ ወደ ኢዮሣፍጥ “የሞዓብ ንጉሥ ዐምዖብኛልና ከእኔ ጋር በሞዓብ ላይ ለሰልፍ ትሄዳለህን?” ብሎ ላከ። እርሱም “እወጣለሁ፤ እኔ እንደ አንተ፥ ሕዝቤም እንደ ሕዝብህ፥ ፈረሶቼም እንደ ፈረሶችህ ናቸው፤” አለ። 8ደግሞም “በምን መንገድ እንሄዳለን?” አለ፤ እርሱም “በኤዶምያስ ምድረ በዳ መንገድ፤” ብሎ መለሰ።
9የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ የኤዶምያስም ንጉሥ ሄዱ፤ የሰባትም ቀን መንገድ ዞሩ፤ ለሠራዊቱና ለተከተሉአቸውም እንስሶች ውሃ አልተገኘም። 10የእስራኤልም ንጉሥ “ወዮ! እግዚአብሔር በሞዓብ እጅ አሳልፎ ይሰጣቸው ዘንድ እነዚህን ሦስቱን ነገሥታት ጠርቶአልና ወዮ!” አለ። 11ኢዮሣፍጥም “በእርሱ እግዚአብሔርን የምንጠይቅበት የእግዚአብሔር ነቢይ በዚህ አይገኝምን?” አለ። ከእስራኤልም ንጉሥ ባሪያዎች አንዱ “በኤልያስ እጅ ላይ ውሃ ያፈስስ የነበረው የሣፋጥ ልጅ ኤልሳዕ እዚህ አለ፤” ብሎ መለሰ። 12ኢዮሣፍጥም “የእግዚአብሔር ቃል በእርሱ ዘንድ ይገኛል፤” አለ። የእስራኤል ንጉሥና ኢዮሣፍጥ የኤዶምያስም ንጉሥ ወደ እርሱ ወረዱ።
13ኤልሳዕም የእስራኤልን ንጉሥ “እኔ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? ወደ አባትህና ወደ እናትህ ነቢያት ሂድ፤” አለው። የእስራኤልም ንጉሥ “አይደለም፥ በሞዓብ እጅ ይጥላቸው ዘንድ እግዚአብሔር እነዚህን ሦስት ነገሥታት ጠርቶአል፤” አለው። 14ኤልሳዕም “በፊቱ የቆምሁት የሠራዊት ጌታ ሕያው እግዚአብሔርን! የይሁዳን ንጉሥ ኢዮሣፍጥን ያላፈርሁ ብሆን ኖሮ አንተን ባልተመለከትሁና ባላየሁ ነበር። 15አሁንም ባለ በገና አምጡልኝ፤” አለ። ባለ በገናውም በደረደረ ጊዜ የእግዚአብሔር እጅ መጣችበት፤ 16እንዲህም አለ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ‘በዚህ ሸለቆ ሁሉ ጕድጓድ ቆፍሩ።’ 17እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ‘ነፋስ አታዩም፤ ዝናብም አታዩም፤ ይህ ሸለቆ ግን ውሃ ይሞላል፤ እናንተም ከብቶቻችሁም እንስሶቻችሁም ትጠጣላችሁ።’ 18ይህም በእግዚአብሔር ዐይን ቀላል ነገር ነው፤ ደግሞም ሞዓባውያንን በእጃችሁ አሳልፎ ይሰጣል። 19የተመሸጉትንና ያማሩትን ከተሞች ሁሉ ትመታላችሁ፤ የሚያፈሩትንም ዛፎች ሁሉ ትቈርጣላችሁ፤ የውሃውንም ምንጮች ሁሉ ትደፍናላችሁ፤ መልካሞችንም እርሻዎች ሁሉ በድንጋይ ታበላሻላችሁ።” 20በነጋውም የቍርባን ጊዜ ሲደርስ፥ እነሆ፥ ውሃ በኤዶምያስ መንገድ መጣ፤ ምድሪቱም ውሃ ሞላች።
21ሞዓባውያንም ሁሉ ነገሥታት ሊወጉአቸው እንደ መጡ በሰሙ ጊዜ በወገባቸው ሰይፍ የሚታጠቁ ሁሉ ተሰበሰቡ፤ ወጥተውም በአገሩ ድንበር ላይ ቆሙ። 22ማልደውም ተነሡ፤ ፀሐይም በውሃው ላይ አንጸባረቀ፤ ሞዓባውያንም በፊታቸው ውሃው እንደ ደም ቀልቶ አዩና “ይህ ደም ነው፤ 23በእርግጥ ነገሥታት እርስ በርሳቸው ተዋጉ፤ እርስ በርሳቸውም ተጋደሉ፤ ሞዓብ ሆይ! እንግዲህ ወደ ምርኮህ ሂድ፤” አሉ። 24ወደ እስራኤል ሰፈር በመጡ ጊዜ እስራኤላውያን ተነሥተው ሞዓባውያንን መቱ፤ እነርሱም ከፊታቸው ሸሹ፤ ሞዓባውያንንም እየመቱ ወደ አገሩ ውስጥ ገቡ። 25ከተሞችንም አፈረሱ፤ በመልካሞቹም እርሻዎች ሁሉ ላይ እስኪሞሉ ድረስ እያንዳንዱ ሰው አንድ አንድ ድንጋይ ይጥል ነበር፤ የውሃውንም ምንጮች ሁሉ ደፈኑ፤ የሚያፈሩትንም ዛፎች ሁሉ ቈረጡ፤ የቂርሐራሴትን ድንጋዮች ብቻ አስቀሩ፤ ባለ ወንጭፎች ግን ከብበው መቱአት። 26የሞዓብም ንጉሥ ሰልፍ እንደ በረታበት ባየ ጊዜ ሰይፍ የሚመዝዙ ሰባት መቶ ሰዎች ከእርሱ ጋር ወሰደ፤ ወደ ኤዶምያስም ንጉሥ ያልፉ ዘንድ ሞከሩ፤ አልቻሉምም። 27በዚያም ጊዜ በእርሱ ፋንታ ንጉሥ የሚሆነውን የበኵር ልጁን ወስዶ ለሚቃጠል መሥዋዕት በቅጥሩ ላይ አቀረበው። በእስራኤልም ዘንድ ታላቅ ቍጣ ሆነ፤ ከዚያም ርቀው ወደ ምድራቸው ተመለሱ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ