እንዲህም ሆነ፤ እግዚአብሔር ኤልያስን በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ ሊያወጣው በወደደ ጊዜ፥ ኤልያስ ከኤልሳዕ ጋር ከጌልገላ ተነሣ። ኤልያስም ኤልሳዕን “እግዚአብሔር ወደ ቤቴል ልኮኛልና በዚህ ቆይ፤” አለው። ኤልሳዕም “ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፤ አልለይህም፤” አለ። ወደ ቤቴልም ወረዱ። በቤቴልም የነበሩ የነቢያት ልጆች ወደ ኤልሳዕ ወጥተው “እግዚአብሔር ጌታህን ከራስህ ላይ ዛሬ እንዲወስደው አውቀሃልን?” አሉት። እርሱም “አዎን፥ አውቄአለሁ፤ ዝም በሉ፤” አላቸው። ኤልያስም “ኤልሳዕ ሆይ! እግዚአብሔር ወደ ኢያሪኮ ልኮኛልና እባክህ፥ በዚህ ቆይ፤” አለው። እርሱም “ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፤ አልለይህም” አለ። ወደ ኢያሪኮም መጡ። በኢያሪኮም የነበሩ የነቢያት ልጆች ወደ ኤልሳዕ ቀርበው “እግዚአብሔር ጌታህን ከራስህ ላይ ዛሬ እንዲወስደው አውቀሃልን?” አሉት። እርሱም “አዎን፥ አውቄአለሁ፤ ዝም በሉ፤” ብሎ መለሰ። ኤልያስም “እግዚአብሔር ወደ ዮርዳኖስ ልኮኛልና እባክህ፥ በዚህ ቆይ፤” አለው። እርሱም “ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፤ አልለይህም፤” አለ። ሁለቱም ሄዱ። ከነቢያትም ልጆች አምሳ ሰዎች ሄዱ፤ በፊታቸውም ርቀው ቆሙ፤ እነዚህም ሁለቱ በዮርዳኖስ ዳር ቆመው ነበር። ኤልያስም መጎናጸፊያውን ወስዶ ጠቀለለው፤ ውሃውንም መታ፤ ወዲህና ወዲያም ተከፈለ፤ ሁለቱም በደረቅ ተሻገሩ። ከተሻገሩም በኋላ ኤልያስ ኤልሳዕን “ከአንተ ሳልወሰድ አደርግልህ ዘንድ የምትሻውን ለምን፤” አለው፤ ኤልሳዕም “መንፈስህ በእኔ ላይ ሁለት እጥፍ ይሆን ዘንድ እለምንሃለሁ፤” አለ። እርሱም “አስቸጋሪ ነገር ለምነሃል፤ ነገር ግን ከአንተ ዘንድ በተወሰድሁ ጊዜ ብታየኝ ይሆንልሃል፤ አለዚያ ግን አይሆንልህም፤” አለ። ሲሄዱም፥ እያዘገሙም ሲጫወቱ፥ እነሆ፥ የእሳት ሠረገላና የእሳት ፈረሶች በመካከላቸው ገብተው ከፈሉአቸው፤ ኤልያስም በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ ወጣ። ኤልሳዕም አይቶ፥ “አባቴ አባቴ ሆይ! የእስራኤል ሠረገላና ፈረሰኞች!” ብሎ ጮኸ። ከዚያም ወዲያ አላየውም፤ ልብሱንም ይዞ ከሁለት ተረተረው። ከኤልያስም የወደቀውን መጎናጸፊያ አነሣ፤ ተመልሶም በዮርዳኖስ ዳር ቆመ። ከኤልያስም የወደቀውን መጎናጸፊያ ወስዶ ውሃውን መታና፥ “የኤልያስ አምላክ እግዚአብሔር ወዴት ነው?” አለ፤ ውሃውንም በመታ ጊዜ ወዲህና ወዲያ ተከፈለ፤ ኤልሳዕም ተሻገረ። ከኢያሪኮም መጥተው በአንጻሩ የነበሩት የነቢያት ልጆች ባዩት ጊዜ “የኤልያስ መንፈስ በኤልሳዕ ላይ ዐርፎአል፤” አሉ። ሊገናኙትም መጥተው በፊቱ ወደ ምድር ተደፋ።
ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 2 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 2:1-15
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos