ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 15
15
አዛርያስ በይሁዳ እንደ ነገሠ
(2ዜ.መ. 25፥1-2)
1በእስራኤል ንጉሥ በኢዮርብዓም በሃያ ሰባተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የአሜስያስ ልጅ ዓዛርያስ*1* ነገሠ። 2መንገሥም በጀመረ ጊዜ የዐሥራ ስድስት ዓመት ልጅ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም አምሳ ሁለት ዓመት ነገሠ፤ እናቱም ይኮልያ የተባለች የኢየሩሳሌም ሴት ነበረች። 3አባቱ አሜስያስ እንዳደረገው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ። 4ነገር ግን በኮረብቶች ላይ ያሉት መስገጃዎች አልተወገዱም፤ ሕዝቡም ገና በኮረብቶች ላይ ባሉት መስገጃዎች ይሠዋና ያጥን ነበር። 5እግዚአብሔርም ንጉሡን ቀሠፈው፤ እስከሚሞትበትም ቀን ድረስ ለምጻም ሆነ፤ በተለየ ቤትም ይቀመጥ ነበር፤ የንጉሡም ልጅ ኢዮአታም በንጉሥ ቤት ላይ ሠልጥኖ ለአገሩ ሕዝብ ይፈርድ ነበር። 6የቀረውም የዓዛርያስ ነገር፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 7ዓዛርያስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ ከአባቶቹ ጋር ቀበሩት፤ ልጁም ኢዮአታም በእርሱ ፋንታ ነገሠ።#15፥7 “ዓዛርያስ” ሌላ ሴሙ ዖዝያን ነው።
ዘካርያስ በእስራኤል እንደ ነገሠ
8በይሁዳ ንጉሥ በዓዛርያስ በሠላሳ ስምንተኛው ዓመት የኢዮርብዓም ልጅ ዘካርያስ በእስራኤል ላይ በሰማርያ ስድስት ወር ነገሠ። 9አባቶቹም እንዳደረጉት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ እስራኤልን ካሳታቸው ከናባጥ ልጅ ከኢዮርብዓም ኀጢአት አልራቀም። 10የኢያቤስም ልጅ ሰሎም ተማማለበት፤ በይብልዓም መትቶ ገደለው፤ በእርሱም ፋንታ ነገሠ። 11የቀረውም የዘካርያስ ነገር፥ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል። 12ለኢዩ “ልጆችህ እስከ አራት ትውልድ ድረስ በእስራኤል ዙፋን ላይ ይቀመጣሉ፤” ተብሎ የተነገረው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነበረ፤ እንዲሁም ሆነ።
ሰሎም በእስራኤል አደነገሠ
13በይሁዳ ንጉሠ በዖዝያን በሠላሳ ዘጠነኛው ዓመት የኢያቤስ ልጅ ሰሎም ነገሠ፤ በሰማርያም አንድ ወር ያህል ነገሠ። 14የጋዲም ልጅ ምናሔም ከቴርሳ ወጥቶ ወደ ሰማርያ መጣ፤ በሰማርያም የኢያቤስን ልጅ ሰሎምን መታ፤ ገደለውም፤ በእርሱም ፋንታ ነገሠ። 15የቀረውም የሰሎም ነገር፥ የተማማለውም ዐመፅ፤ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል። 16በዚያን ጊዜም ምናሔም ከቴርሳ ወጥቶ ቲፍሳን በእርስዋም ያሉትን ሁሉ ዳርቻዋንም መታ፤ ይከፍቱለትም ዘንድ አልወደዱምና መታት፤ በእርስዋም የነበሩትን እርጉዞች ሁሉ ቀደዳቸው።
ምናሔም በእስራኤል እንደ ነገሠ
17በይሁዳ ንጉሥ በዓዛርያስ በሠላሳ ዘጠነኛው ዓመት የጋዲ ልጅ ምናሔም በእስራኤል ላይ መንገሠ ጀመረ፤ በሰማርያም ዐሥር ዓመት ነገሠ። 18በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ እስራኤልን ካሳተው ከናባጥ ልጅ ከኢዮርብዓም ኀጢአት አልራቀም። 19በዘመኑም የአሦር ንጉሥ ፎሐ በምድሪቱ ላይ ወጣ፤ ምናሔምም መንግሥቱን በእጁ ያጸናለት ዘንድ የፎሐ እጅ ከእርሱ ጋር እንዲሆን አንድ ሺህ መክሊት ብር ሰጠው። 20ምናሔምም ብሩን ለአሦር ንጉሥ ይሰጥ ዘንድ በእስራኤል ባለ ጠጎች ሁሉ ላይ በእያንዳንዱ ላይ አምሳ ሰቅል ብር አስገብሮ አወጣ። የአሦርም ንጉሥ ተመለሰ፤ በአገሪቱም አልተቀመጠም። 21የቀረውም የምናሔም ነገር፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 22ምናሔም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ልጁም ፋቂስያስ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።
ፋቂስያስ በእስራኤል እንደ ነገሠ
23በይሁዳ ንጉሥ በዓዛርያስ በአምሳኛው ዓመት የምናሔም ልጅ ፋቂስያስ በእስራኤል ላይ በሰማርያ መንገሥ ጀመረ፤ ሁለት ዓመትም ነገሠ። 24በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ እስራኤልን ካሳተው ከናባጥ ልጅ ከኢዮርብዓም ኀጢአት አልራቀም። 25የሠራዊቱም አለቃ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ ተማማለበት፤ በሰማርያም በንጉሡ ቤት ግንብ ውስጥ ከአርጎብና ከአርያ ጋር መታው፤ ከእርሱም ጋር አምሳ የገለዓድ ሰዎች ነበሩ፤ ገደለውም፤ በእርሱም ፋንታ ነገሠ። 26የቀረውም የፋቂስያስ ነገር፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ፥ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል።
ፋቁሔ በእስራኤል እንደ ነገሠ
27በይሁዳ ንጉሥ በዓዛርያስ በአምሳ ሁለተኛው ዓመት የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ በእስራኤል ላይ በሰማርያ መንገሥ ጀመረ፤ ሃያ ዓመትም ነገሠ። 28በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ እስራኤልን ካሳተው ከናባጥ ልጅ ከኢዮርብዓም ኀጢአት አልራቀም።
29በእስራኤልም ንጉሥ በፋቁሔ ዘመን የአሦር ንጉሥ ቴልጌልቴልፌልሶር መጥቶ ዒዮንና አቤልቤትመዓካን፥ ያኖዋንም፥ ቃዴስንና አሶርንም፥ ገለዓድንና ገሊላንም፥ የንፍታሌምን አገር ሁሉ ወሰደ፤ ወደ አሦርም አፈለሳቸው። 30በዖዝያንም ልጅ በኢዮአታም በሀያኛው ዓመት የኤላ ልጅ ሆሴዕ በሮሜልዩ ልጅ በፋቁሔ ላይ ተማማለ፤ መትቶም ገደለው፤ በእርሱም ፋንታ ነገሠ። 31የቀረውም የፋቁሔ ነገር፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ፥ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል።
ኢዮአታም በይሁዳ እንደ ነገሠ
(2ዜ.መ. 27፥1-9)
32በእስራኤል ንጉሥ በሮሜልዩ ልጅ በፋቁሔ በሁለተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የዖዝያን ልጅ ኢዮአታም ነገሠ። 33መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሃያ አምስት ዓመት ጐልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ዐሥራ ስድስት ዓመት ነገሠ፤ እናቱ የሳዶቅ ልጅ ኢየሩሳ ነበረች። 34በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ፤ አባቱ ዖዝያን እንዳደረገ ሁሉ እንዲሁ አደረገ። 35ነገር ግን በኮረብቶች ላይ ያሉት መስገጃዎች አልተወገዱም፤ ሕዝቡም ገና በኮረብቶች ላይ ባሉት መስገጃዎች ይሠዋና ያጥን ነበር። እርሱም የላይኛውን የእግዚአብሔርን ቤት በር ሠራ። 36የቀረውም የኢዮአታም ነገር፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 37በዚያም ወራት እግዚአብሔር የሶርያን ንጉሥ ረአሶንንና የሮሜልዩን ልጅ ፋቁሔን በይሁዳ ላይ መስደድ ጀመረ። 38ኢዮአታም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በአባቱም በዳዊት ከተማ ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ፤ ልጁም አካዝ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 15: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ