ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 14
14
አሜስያስ በይሁዳ እንደ ነገሠ
(2ዜ.መ. 25፥1-24)
1በእስራኤል ንጉሥ በኢዮአካዝ ልጅ በዮአስ በሁለተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የኢዮአስ ልጅ አሜስያስ ነገሠ። 2መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ አምስት ዓመት ጐልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሃያ ዘጠኝ ዓመት ነገሠ። እናቱም ዮዓዳን የተባለች የኢየሩሳሌም ሴት ነበረች። 3በእግዚአብሔርም ፊት ቅን ነገር አደረገ፤ ነገር ግን አባቱ ኢዮአስ እንዳደረገ ሁሉ እንጂ እንደ አባቱ እንደ ዳዊት አላደረገም። 4ነገር ግን በኮረብቶቹ ላይ ያሉት መስገጃዎች አልተወገዱም፤ ሕዝቡም ግና በኮረብቶች ላይ ባሉት መስገጃዎች ይሠዋና ያጥን ነበር። 5መንግሥቱም በጸናለት ጊዜ አባቱን የገደሉትን ባሪያዎች ገደለ። 6በሙሴ ሕግ መጽሐፍም እንደ ተጻፈ፥ እግዚአብሔርም “ሁሉ በኀጢአቱ ይሙት እንጂ አባቶች በልጆች አይሙቱ፤ ልጆችም በአባቶች አይሙቱ፤” ብሎ እንዳዘዘ የነፍሰ ገዳዮቹን ልጆች አልገደለም። 7እርሱም በጨው ሸለቆ ከኤዶምያስ ዐሥር ሺህ ሰው ገደለ፤ ሴላን በሰልፍ ወስዶ ስምዋን እስከ ዛሬ ድረስ ዮቅትኤል ብሎ ጠራት።
8በዚያን ጊዜም አሜስያስ “ና፤ እርስ በርሳችን ፊት ለፊት እንተያይ፤” ብሎ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ ኢዩ ልጅ ወደ ኢዮአካዝ ልጅ ወደ ዮአስ መልእክተኞችን ላከ። 9የእስራኤልም ንጉሥ ዮአስ “የሊባኖስ ኵርንችት፥ ‘ልጅህን ለልጄ ሚስት አድርገህ ስጠው፤’ ብሎ ወደ ሊባኖስ ዝግባ ላከ፤ የሊባኖስም አውሬ አልፎ ኵርንችቱን ረገጠ። 10ኤዶምያስን በእውነት መታህ፤ ልብህንም ከፍ ከፍ አደረግህ፤ በዚያ ድል ተመካ፤ በቤትህም ተቀመጥ፤ አንተ ከይሁዳ ጋር ትወድቅ ዘንድ ስለ ምን መከራ ትሻለህ?” ብሎ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሜስያስ ላከ።
11አሜስያስ ግን አልሰማም፤ የእስራኤልም ንጉሥ ዮአስ ወጣ፤ እርሱና የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስም በይሁዳ ባለች በቤት ሳሚስ እርስ በርሳቸው ተያዩ። 12ይሁዳም በእስራኤል ፊት ተመታ፤ እያንዳንዱም ወደ ድንኳኑ ሸሸ። 13የእስራኤልም ንጉሥ ዮአስ የይሁዳን ንጉሥ የአካዝያስን ልጅ የኢዮአስን ልጅ አሜስያስን በቤትሳሚስ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፤ የኢየሩሳሌምንም ቅጥር ከኤፍሬም በር ጀምሮ እስክ ማዕዘኑ በር ድረስ አራት መቶ ክንድ አፈረሰ። 14ወርቁንና ብሩን ሁሉ፥ በእግዚአብሔርም ቤትና በንጉሡ ቤት መዛግብት የነበሩትን ዕቃዎች ሁሉ፥ በመያዣም የተያዙትን ወስዶ ወደ ሰማርያ ተመለሰ።
15የቀረውም ያደረገው የዮአስ ነገር፥ ጭከናውም፥ ከይሁዳም ንጉሥ ከአሜስያስ ጋር እንደ ተዋጋ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 16ዮአስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በሰማርያም ከእስራኤል ነገሥታት ጋር ተቀበረ፤ ልጁም ኢዮርብዓም በፋንታው ነገሠ።
የይሁዳ ንጉሥ የአሜስያስ መሞት
(2ዜ.መ. 25፥25-28)
17የይሁዳም ንጉሥ የኢዮአስ ልጅ አሜስያስ ከእስራኤል ንጉሥ ከኢዮአካዝ ልጅ ከዮአስ ሞት በኋላ ዐሥራ አምስት ዓመት ኖረ። 18የቀረውም የአሜስያስ ነገር በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 19በኢየሩሳሌምም የዐመፅ መሐላ አደረጉበት፤ እርሱም ወደ ለኪሶ ኮበለለ፤ በኋላውም ወደ ለኪሶ ላኩ፤ በዚያም ገደሉት። 20በፈረስም ጭነው አመጡት፤ በኢየሩሳሌምም በዳዊት ከተማ ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ። 21የይሁዳም ሕዝብ ሁሉ የዐሥራ ስድስት ዓመት ልጅ የነበረውን ዓዛርያስን ወስዶ በአባቱ በአሜስያስ ፋንታ አነገሠው። 22ንጉሡም ከአባቶቹ ጋር ካንቀላፋ በኋላ፥ ኤላትን ሠርቶ ወደ ይሁዳ መለሳት።
ዳግማዊ ኢዮርበዓም በእስራኤል እንደ ነገሠ
23በይሁዳ ንጉሥ በኢዮአስ ልጅ በአሜስያስ በዐሥራ አምስተኛው ዓመት የእስራኤል ንጉሥ የዮአስ ልጅ ኢዮርብዓም በሰማርያ መንገሥ ጀመረ፤ አርባ አንድ ዓመትም ነገሠ። 24በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ እስራኤልንም ካሳተው ከናባጥ ልጅ ከኢዮርብዓም ኀጢአት ሁሉ አልራቀም። 25የጋትሔፌር በነበረው በአማቴ ልጅ በባሪያው በነቢዩ በዮናስ እንደ ተናገረው እንደ እስራኤል አምላክ እንደ እግዚአብሔር ቃል የእስራኤልን ድንበር ከሐማት መግቢያ ጀምሮ እስከ ዓረባ ባሕር ድረስ መለሰ። 26የታሰረውና የተለቀቀውም እንደ ጠፋ፥ እስራኤልንም የሚረዳ እንዳልነበረ እግዚአብሔር እጅግ የመረረውን የእስራኤልን ጭንቀት አየ። 27እግዚአብሔርም የእስራኤልን ስም ከሰማይ በታች ይደመስስ ዘንድ አልተናገረም፤ ነገር ግን በዮአስ ልጅ በኢዮርብዓም እጅ አዳናቸው።
28የቀረውም የኢዮርብዓም ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ ጭከናውም፥ እንደ ተዋጋም፥ የይሁዳ የነበረውን ደማስቆንና ሐማትን ለእስራኤል እንደ መለሰ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 29ኢዮርብዓምም ከአባቶቹ ከእስራኤል ነገሥታት ጋር አንቀላፋ፤ ልጁም ዘካርያስ በፋንታው ነገሠ።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 14: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ