ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 1
1
ኤልያስና ንጉሥ አካዝያስ
1አክዓብ ከሞተ በኋላ ሞዓብ በእስራኤል ላይ ዐመፀ። 2አካዝያስም በሰማርያ በሰገነቱ ላይ ሳለ ከዐይነ ርግቡ ወድቆ ታመመ፤ እርሱም “ሂዱ፤ ከዚህም ደዌ እድን እንደ ሆነ የአቃሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን ጠይቁ፤” ብሎ መልእክተኞችን ላከ። 3የእግዚአብሔርም መልአክ ቴስብያዊውን ኤልያስን “ተነሣ፤ የሰማርያን ንጉሥ መልእክተኞች ለመገናኘት ውጣና ‘የአቃሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን ትጠይቁ ዘንድ የምትሄዱት በእስራኤል ዘንድ አምላክ ስለሌለ ነውን? 4ስለዚህም እግዚአብሔር እንዲህ ይላል “ትሞታለህ እንጂ ከወጣህበት አልጋ አትወርድም፤” በላቸው’” አለው። ኤልያስም ሄደ።
5መልእክተኞችም ወደ አካዝያስ ተመለሱ፤ እርሱም “ለምን ተመለሳችሁ?” አላቸው። 6እነርሱም “አንድ ሰው ሊገናኘን መጣና ‘ሂዱ፤ ወደ ላካችሁም ንጉሥ ተመልሳችሁ” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል የአቃሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን ትጠይቅ ዘንድ የላከህ በእስራኤል ዘንድ አምላክ ስለሌለ ነውን? ስለዚህ ትሞታለህ እንጂ ከወጣህበት አልጋ አትወርድም፤” በሉት፤’ አለን፤” አሉት። 7እርሱም “ሊገናኛችሁ የወጣው፥ ይህንስ ቃል የነገራችሁ ሰው መልኩ ምን ይመስላል?” አላቸው። 8እነርሱም “ሰውዮው ጠጕራም ነው፤ በወገቡም ጠፍር ታጥቆ ነበር፤” አሉት። እርሱም “ቴስብያዊው ኤልያስ ነው፤” አለ።
9ንጉሡም የአምሳ አለቃውን ከአምሳ ሰዎች ጋር ሰደደ፤ ወደ እርሱም ወጣ፤ እነሆም፥ በተራራ ራስ ላይ ተቀምጦ ነበር። እርሱም “የእግዚአብሔር ሰው ሆይ! ንጉሡ ‘ውረድ’ ይልሃል፤” አለው። 10ኤልያስም መልሶ የአምሳ አለቃውን “እኔስ የእግዚአብሔር ሰው እንደ ሆንሁ እሳት ከሰማይ ትውረድ፤ አንተንም፥ አምሳውንም ሰዎችህን ትብላ፤” አለው። እሳትም ከሰማይ ወርዳ እርሱንና አምሳ ሰዎቹን በላች። 11ደግሞም ሌላ የአምሳ አለቃ ከአምሳ ሰዎች ጋር ላከበት፤ እርሱም “የእግዚአብሔር ሰው ሆይ! ንጉሡ ‘ፈጥነህ ውረድ’ ይላል፤” ብሎ ተናገረ። 12ኤልያስም “እኔስ የእግዚአብሔር ሰው እንደ ሆንሁ እሳት ከሰማይ ትውረድ፤ አንተንም፥ አምሳውንም ሰዎችህን ትብላ፤” አለው። የእግዚአብሔርም እሳት ከሰማይ ወርዳ እርሱንና አምሳ ሰዎቹን በላች። 13ደግሞም ሦስተኛ የአምሳ አለቃ ከአምሳ ሰዎች ጋር ሰደደ፤ ሦስተኛውም የአምሳ አለቃ ወጥቶ በኤልያስ ፊት በጕልበቱ ተንበረከከና “የእግዚአብሔር ሰው ሆይ! ነፍሴና የእነዚህ የአምሳው ባሪያዎችህ ነፍስ በፊትህ የከበረች ትሁን። 14እነሆ፥ እሳት ከሰማይ ወርዳ የፊተኞቹን ሁለቱን የአምሳ አለቆችና አምሳ አምሳፍ ሰዎቻቸውን በላች፤ አሁን ግን ነፍሴ በፊትህ የከበረች ትሁን፤” ብሎ ለመነው። 15የእግዚአብሔርም መልአክ ኤልያስን “ከእርሱ ጋር ውረድ፤ አትፍራውም፤” አለው። ተነሥቶም ከእርሱ ጋር ወደ ንጉሡ ወረደ። 16ኤልያስም “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ‘የአቃሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን ትጠይቅ ዘንድ መልእክተኞችን ልከሃልና ትሞታለህ እንጂ ከወጣህበት አልጋ አትወርድም’” አለው።
17ኤልያስም እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል አካዝያስ ሞተ። ልጅም አልነበረውምና በይሁዳ ንጉሥ በኢዮሣፍጥ ልጅ በኢዮራም በሁለተኛው ዓመት ወንድሙ ኢዮራም በእርሱ ፋንታ ነገሠ። 18አካዝያስ ያደረገው የቀረው ነገር በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 1: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ