እንደ ንጉሡም እንደ ኢዮስያስ ትእዛዝ በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ያቀርቡ ዘንድ፥ ፋሲካውንም ያደርጉ ዘንድ የእግዚአብሔር አገልግሎት ሁሉ በዚያ ቀን ተዘጋጀ። የተገኙትም የእስራኤል ልጆች በዚያ ቀን ፋሲካውን፥ ሰባት ቀንም የቂጣ በዓልን አደረጉ። ከነቢዩ ከሳሙኤል ዘመን ጀምሮ እንደዚህ ያለ ፋሲካ በእስራኤል ዘንድ ከቶ አልተደረገም፤ ከእስራኤልም ነገሥታት ሁሉ ኢዮስያስና ካህናቱ፥ ሌዋውያኑም፥ በዚያም የተገኙ የይሁዳና የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ፥ በኢየሩሳሌምም የሚኖሩት እንዳደረጉት ያለ ፋሲካ ያደረገ የለም። ይህም ፋሲካ ኢዮስያስ በነገሠ በአሥራ ስምንተኛው ዓመት ተደረገ። ከዚህም ሁሉ በኋላ፥ ኢዮስያስም ቤተ መቅደሱን ካሰናዳ በኋላ፥ የግብጽ ንጉሥ ኒካዑ በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ ባለው በከርከሚሽ ላይ ይዋጋ ዘንድ ወጣ፤ ኢዮስያስም ሊጋጠመው ወጣ። እርሱም “የይሁዳ ንጉሥ ሆይ! ከአንተ ጋር ምን አለኝ? በምዋጋበት በሌላ ቤት ላይ ነው እንጂ በአንተ ላይ ዛሬ አልመጣሁም፤ እግዚአብሔርም እንድቸኵል አዝዞኛል፤ ከእኔ ጋር ያለው እግዚአብሔር እንዳያጠፋህ ይህን በእርሱ ላይ ከማድረግ ተመለስ” ብሎ መልእክተኞችን ላከበት። ኢዮስያስ ግን ይዋጋው ዘንድ ተጸናና እንጂ ፊቱን ከእርሱ አልመለሰም፤ በእግዚአብሔርም አፍ የተነገረውን የኒካዑን ቃል አልሰማም፥ በመጊዶም ሸለቆ ይዋጋ ዘንድ መጣ። ቀስተኞችም ንጉሡን ኢዮስያስን ወጉት፤ ንጉሡም ብላቴናዎቹን “አጥብቄ ቆስያለሁና ከሰልፉ ውስጥ አውጡኝ” አላቸው። ብላቴናዎቹም ከሠረገላው አውርደው ለእርሱ በነበረው በሁለተኛው ሠረገላ ውስጥ አስቀመጡት፤ ወደ ኢየሩሳሌምም አመጡት፤ እርሱም ሞተ፤ በአባቶቹም መቃብር ተቀበረ፤ ይሁዳና ኢየሩሳሌምም ሁሉ ለኢዮስያስ አለቀሱ። ኤርምያስም ለኢዮስያስ የልቅሶ ግጥም ገጠመለት፤ እስከ ዛሬም ድረስ ወንዶችና ሴቶች መዘምራን ሁሉ በልቅሶ ግጥማቸው ስለ ኢዮስያስ ይናገሩ ነበር፤ ይህም በእስራኤል ዘንድ ወግ ሆኖ በልቅሶ ግጥም ተጽፎአል። የቀረውም የኢዮስያስ ነገር፥ በእግዚአብሔርም ህግ እንደተጻፈ ያደረገው ቸርነት፥ የፊተኛውና የኋለኛውም ነገሩ፥ እነሆ፥ በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፎአል።
ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 35 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 35:16-27
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች