ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 33
33
ምናሴ በይሁዳ እንደነገሠ (2 ነገ21፥1-9፥17-18)
1ምናሴም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የአሥራ ሁለት ዓመት ልጅ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም አምሳ አምስት ዓመት ነገሠ። 2እግዚአብሔርም ከእስራኤል ልጆች ፊት እንዳወጣቸው እንደ አሕዛብ ያለ ርኵሰት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ። 3አባቱም ሕዝቅያስ ያፈረሳቸውን የኮረብታውን መስገጃዎች መልሶ ሠራ፤ ለበኣሊምም መሠዊያ ሠራ፤ የማምለኪያ ዐፀዶችንም ተከለ፤ ለሰማይም ሠራዊት ሁሉ ሰገደ፤ አመለካቸውም። 4እግዚአብሔርም “ስሜ በኢየሩሳሌም ለዘላለም ይኖራል” ባለው በእግዚአብሔር ቤት መሠዊያዎችን ሠራ። 5በእግዚአብሔርም ቤት በሁለቱ አደባባዮች ላይ ለሰማይ ሠራዊት ሁሉ መሠዊያዎችን ሠራ። 6በሄኖምም ልጅ ሸለቆ ውስጥ ልጆቹን በእሳት አሳለፈ፤ ሞራ ገላጭም ሆነ፤ አስማትም አደረገ፤ መተተኛም ነበረ፤ መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቍዮችንም ሰበሰበ፤ ያስቈጣውም ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ክፉ ነገር አደረገ። 7-8እግዚአብሔርም ለዳዊትና ለልጁ ለሰሎሞን “በዚህ ቤት ከእስራኤልም ነገድ ሁሉ በመረጥኋት በኢየሩሳሌም ስሜን ለዘላለም አኖራለሁ፤ ያዘዝኋቸውንም ሁሉ፥ በሙሴ የተሰጠውን ሕግና ሥርዓት ፍርድንም ሁሉ ቢያደርጉ፥ ቢጠብቁም፥ ለአባቶቻችሁ ከሰጠኋት ምድር የእስራኤልን እግር እንደ ገና አላርቅም፤” ባለበት በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ የሠራውን የጣዖት፥ የተቀረጸውን ምስል አቆመ። 9ምናሴም እግዚአብሔር ከእስራኤል ልጆች ፊት ካጠፋቸው ከአሕዛብ ይልቅ ክፉ ይሠሩ ዘንድ በይሁዳና በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን አሳተ።
ምናሴ ከኃጢያቱ እንደተመለሠ
10እግዚአብሔርም ምናሴንና ሕዝቡን ተናገራቸው፤ ግን አልሰሙትም። 11ስለዚህም እግዚአብሔር የአሦርን ንጉሥ ሠራዊት አለቆች አመጣባቸው፤ ምናሴንም በዛንጅር ያዙት፤ በሰንሰለትም አስረው ወደ ባቢሎን ወሰዱት። 12በተጨነቀም ጊዜ አምላኩን እግዚአብሔርን ፈለገ፤ በአባቶቹም አምላክ ፊት ሰውነቱን እጅግ አዋረደ፤ 13ወደ እርሱም ጸለየ፤ እርሱም ተለመነው፤ ጸሎቱንም ሰማው፤ ወደ መንግሥቱም ወደ ኢየሩሳሌም መለሰው፤ ምናሴም እግዚአብሔር እርሱ አምላክ እንደ ሆነ አወቀ።
14ከዚህ በኋላ በዳዊት ከተማ በስተ ውጭው ከግዮን ምዕራብ በሸለቆው ውስጥ እስከ ዓሳ በር መግቢያ ድረስ ቅጥር ሠራ። በዖፌልም አዞረበት፤ እጅግም ከፍ አደረገው፤ በተመሸጉትም በይሁዳ ከተሞች ሁሉ የጭፍራ አለቆችን አኖረ። 15እንግዶችንም አማልክትና ጣዖቱንም ከእግዚአብሔር ቤት አራቀ፤ የእግዚአብሔርም ቤት ባለበት ተራራ ላይና በኢየሩሳሌም የሠራቸውን መሠዊያዎች ሁሉ ወስዶ ከከተማይቱ በስተ ውጭ ጣላቸው። 16የእግዚአብሔርንም መሠዊያ ደግሞ አደሰ፤ የደኅንነትንና የምስጋናንም መሥዋዕት ሠዋበት፤ ይሁዳም የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ አዘዘ። 17ሕዝቡ ግን ገና በኮረብታው መስገጃዎች ይሠዋ ነበር፤ ቢሆንም ለአምላኩ ለእግዚአብሔር ብቻ ነበረ።
የምናሴ ዘመነ መንግሥት ፍፃሜ
18የምናሴም የቀረው ነገር፥ ወደ አምላኩም የጸለየው ጸሎት፥ በእስራኤልም አምላክ በእግዚአብሔር ስም የነገሩት የነቢያት ቃል፥ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፎአል። 19ደግሞም ጸሎቱ፥ እግዚአብሔርም እንደ ተለመነው፥ ኃጢያቱና መተላለፉ ሁሉ፥ ራሱንም ሳያዋርድ የኮረብታው መስገጃዎችን የሰራበት የማምለኪያ ዐፀዱንና የተቀረጹትንም ምስሎች የተከለበት ስፍራ፥ እነሆ፥ በባለ ራእዩ ታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል። 20ምናሴም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በቤቱም ቀበሩት፤ ልጁም አሞን በእርሱ ፋንታ ነገሠ።
አሞን በይሁዳ እንደነገሠ (2 ነገ.21፥19-26)
21አሞን መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሃያ ሁለት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሁለት ዓመት ነገሠ። 22አባቱም ምናሴ እንዳደረገ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ፤ አሞንም አባቱ ምናሴ ለሠራቸው ለተቀረጹት ምስሎች ሁሉ ሠዋ፤ አመለካቸውም። 23አባቱም ምናሴ ሰውነቱን እንዳዋረደ በእግዚአብሔር ፊት ሰውነቱን አላዋረደም፤ ነገር ግን አሞን መተላለፉን እጅግ አበዛ። 24ባሪያዎቹም ተማምለው በቤቱ ገደሉት። 25የአገሩ ሕዝብ ግን በንጉሡ በአሞን ላይ የተማማሉትን ሁሉ ገደሉ፤ የአገሩም ሕዝብ ልጁን ኢዮስያስን በእርሱ ፋንታ አነገሡ።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 33: አማ54
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ