ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 32
32
ሰናክሬም ይሁዳን እንደውረረ
(2ነገ. 18፥13-37፤ ኢሳ. 36፥1-22)
1ከዚህም ነገርና ከዚህ እምነት በኋላ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም መጥቶ ወደ ይሁዳ ገባ፤ በተመሸጉትም ከተሞች ፊት ሰፈረ፤ ሊወስዳቸውም አሰበ። 2ሕዝቅያስም ሰናክሬም እንደ መጣ፥ ኢየሩሳሌምንም ሊወጋ ፊቱን አንዳቀና ባየ ጊዜ፥ 3ከከተማይቱ በስተ ውጭ ያለውን የውኃውን ምንጭ ይደፍኑ ዘንድ ከአለቆቹና ከኃያላኑ ጋር ተማከረ፤ እነርሱም ረዱት። 4እጅግም ሰዎች ተሰብስበው “የአሦር ነገሥታት መጥተው ብዙ ውኃ ስለ ምን ያገኛሉ?” ብለው ምንጩን ሁሉ፥ በምድርም መካከል ይንዶለዶል የነበረውን ወንዝ ደፈኑ። 5ሰውነቱንም አጸናና፥ የፈረሰውንም ቅጥር ሁሉ ጠገነ፤ በላዩም ግንብ ሠራበት፤ ከእርሱም በስተ ውጭ ሌላ ቅጥር ሠራ፤ በዳዊትም ከተማ ያለችውን ሚሎን አጠነከረ፤ ብዙም መሣሪያና ጋሻ ሠራ። 6የጦር አለቆቹንም በሕዝቡ ላይ ሾሞ፤ ሁሉንም በከተማይቱ በር ወዳለው አደባባይ ሰብስቦ 7“ጽኑ፤ አይዞአችሁ፤ ከእኛም ጋር ያለው ከእርሱ ጋር ካለው ይበልጣልና ከአሦር ንጉሥና ከእርሱ ጋር ካለው ጭፍራ ሁሉ አትፍሩ፤ አትደንግጡም። 8ከእርሱ ጋር የሥጋ ክንድ ነው፤ ከእኛ ጋር ያለው ግን የሚረዳንና የሚዋጋልን አምላካችን እግዚአብሔር ነው” ብሎ አጽናናቸው። ሕዝቡም በይሁዳ ንጉሥ በሕዝቅያስ ቃል ተጽናና።
9ከዚህም በኋላ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም ከሠራዊቱ ሁሉ ጋር በለኪሶ ፊት ሳለ ባሪያዎቹን ወደ ኢየሩሳሌም ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ሕዝቅያስና በኢየሩሳሌም ወደ ነበሩ ወደ ይሁዳ ሁሉ እንዲህ ሲል ላከ 10“የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም እንዲህ ይላል ‘እናንተ በማን ተማምናችሁ በኢየሩሳሌም ምሽግ ትቀመጣላችሁ? 11“አምላካችን እግዚአብሔር ከአሦር ንጉሥ እጅ ያድነናል” እያለ በራብና በጥም እንድትሞቱ አሳልፎ ይሰጣችሁ ዘንድ የሚያባብላችሁ ሕዝቅያስ አይደለምን? 12“በአንድ መሠዊያ ፊት ስገዱ፤ በእርሱም ላይ ዕጠኑ” እያለ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን አዝዞ፥ የኮረብታው መስገጃዎቹና መሠዊያዎቹን ያፈረሰ ይህ ሕዝቅያስ አይደለምን? 13እኔና አባቶቼ በምድር አሕዛብ ሁሉ ያደረግነውን አላወቃችሁምን? የምድርስ ሁሉ አሕዛብ አማልክት አገራቸውን ከእጄ ያድኑ ዘንድ በውኑ ተቻላቸውን? 14አምላካችሁስ ከእጄ እናንተን ለማዳን ይችል ዘንድ አባቶቼ ካጠፉአቸው ከአሕዛብ አማልክት ሁሉ ሕዝቡን ከእጄ ያድን ዘንድ የቻለ ማን ነው? 15አሁንም ሕዝቅያስ አያስታችሁ፤ እንዲህም አያባብላችሁ፤ አትመኑትም፤ ከአሕዛብና ከመንግስታት አማልክት ሁሉ ሕዝቡን ከእጄና ከአባቶቼ እጅ ያድን ዘንድ ማንም አልቻለም፤ ይልቁንስ አምላካችሁ ከእጄ ያድናችሁ ዘንድ እንዴት ይችላል?’”
16ባሪያዎቹም ደግሞ በአምላክ በእግዚአብሔርና በባሪያው በሕዝቅያስ ላይ ሌላ ብዙ ነገር ተናገሩ። 17ደግሞም የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን ለመስደብ፥ በእርሱም ላይ ለመናገር “የምድር አሕዛብ አማልክት ሕዝባቸውን ከእጄ ያድኑ ዘንድ እንዳልቻሉ፥ እንዲሁ የሕዝቅያስ አምላክ ሕዝቡን ከእጄ ያድን ዘንድ አይችልም” የሚል ደብዳቤ ጻፈ። 18ከተማይቱንም እንዲወስዱ፥ በቅጥር ላይ የተቀመጡትን የኢየሩሳሌም ሕዝብ ያስፈሩና ያስደነግጡ ዘንድ፥ በታላቅ ድምፅ በዕብራይስጥ ቋንቋ ይጮኹባቸው ነበር። 19በሰውም እጅ በተሠሩ በምድር አሕዛብ አማልክት ላይ አንደሚናገሩ መጠን በኢየሩሳሌም አምላክ ላይ ተናገሩ።
የንጉሥ ሰናክሬም ሞት (2ነገ. 19፥14-19፥35-37፤ ኢሳ.37፥14-20፥36-38)
20ንጉሡም ሕዝቅያስና የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስ ስለዚህ ጸለዩ፤ ወደ ሰማይም ጮኹ። 21እግዚአብሔርም ጽኑዓን ኃያላኑንና መሳፍንቱን አለቆቹንም ከአሦር ንጉሥ ሰፈር እንዲያጠፋ መልአኩን ሰደደ። የአሦርም ንጉሥ አፍሮ ወደ አገሩ ተመለሰ። ወደ አምላኩም ቤት በገባ ጊዜ ከወገቡ የወጡት ልጆቹ በዚያ በሰይፍ ገደሉት። 22እንዲሁም እግዚአብሔር ሕዝቅያስንና በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ከአሦር ንጉሥ ከሰናክሬም እጅ ከሁሉም እጅ አዳናቸው፤ በዙሪያቸውም ካለው ሁሉ አሳረፋቸው። 23ብዙዎቹም ለእግዚአብሔር መባ ይዘው ወደ ኢየሩሳሌም ይመጡ ነበር፤ ለይሁዳም ንጉሥ ለሕዝቅያስ እጅ መንሻ ይሰጡ ነበር፤ እርሱም ከዚህ ነገር በኋላ በአሕዛብ ሁሉ ፊት ከፍ ከፍ አለ።
የሕዝቅያስ ከሕመሙ መዳን (2 ነገ.20፥1-11፤ ኢሳ.38፥1-8)
24በዚያም ወራት ሕዝቅያስ እስኪሞት ድረስ ታመመ፤ ወደ እግዚአብሔርም ጸለየ፤ እርሱም ተናገረው፤ ምልክትም ሰጠው። 25ሕዝቅያስ ግን እንደ ተቀበለው ቸርነት መጠን አላደረገም፤ ልቡም ኳራ፤ ስለዚህም በእርሱና በይሁዳ በኢየሩሳሌምም ላይ ቍጣ ሆነ። 26ሕዝቅያስም ከኢየሩሳሌም ሰዎች ጋር ስለ ልቡ ኵራት ሰውነቱን አዋረደ፤ የእግዚአብሔርም ቍጣ በሕዝቅያስ ዘመን አልመጣባቸውም።
የሕዝቅያስ ብልፅግና (2 ነገ.20፥12-19፤ ኢሳ.39፥1-8)
27ለሕዝቅያስም እጅግ ብዙ ሀበትና ክብር ነበረው፤ ለብርና ለወርቅም፥ ለከበረው ዕንቍና ለሽቱው፥ ለጋሻውና ለከበረው ዕቃ ሁሉ ግምጃ ቤቶች ሠራ። 28ለእህልና ለወይን ጠጅም ለዘይትም ዕቃ ቤቶች፥ ለልዩ ልዩም እንሰሳ ጋጥ፥ ለመንጎችም በረት ሠራ። 29እግዚአብሔርም እጅግ ብዙ ጥሪት ሰጥቶት ነበርና ከተሞችን ሠራ፤ ብዙም የበግና የላም መንጋ ሰበሰበ። 30ይህም ሕዝቅያስ የላይኛውን የግዮንን ውኃ ምንጭ ደፈነ፤ በዳዊትም ከተማ በምዕራብ በኩል አቅንቶ አወረደው። የሕዝቅያስም ሥራ ሁሉ ተከናወነ። 31ነገር ግን የባቢሎን መሳፍንት መልእክተኞች በአገሩ ላይ ስለ ተደረገው ተአምራት ይጠይቁት ዘንድ ወደ እርሱ በተላኩ ጊዜ እግዚአብሔር ይፈትነውና በልቡ ያለውን ሁሉ ያውቅ ዘንድ ተወው።
የሕዝቅያስ መሞት (2ነገ. 20፥ 20-21)
32የሕዝቅያስም የቀረው ነገር፥ ቸርነቱም፥ እነሆ፥ በአሞጽ ልጅ በነቢዩ በኢሳይያስ ራእይ በይሁዳና በእስራኤልም ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፎአል። 33ሕዝቅያስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊትም ልጆች መቃብር በላይኛው ክፍል ቀበሩት፤ በይሁዳና በኢየሩሳሌምም የሚኖሩ ሁሉ በሞቱ አከበሩት። ልጁም ምናሴ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 32: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ